Search

አዛውንቶች የሚገደሉበትና ንብረት የሚዘረፍበት ተግባር የትግል ዓላማ ሊሆን አይችልም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 85

የአማራ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተስተዋለ ያለውን እውነታ በስክነት መገምገም እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት፣ በአማራ ክልል በትግል ስም ዜጎች የሚገደሉበት፣ ንብረት የሚዘረፍበት እና የአማራ ህዝብ ልጆቹን ለማስተማር የሚቸገርበት አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ከአማራ ክልልም ሆነ ከኦሮሚያ ወደ ጫካ የገቡ አካላት ያቀረቧቸውን ምክንያቶችና አሁን በመሬት ላይ እየሆነ ያለውን ተጨባጭ እውነታ ቆም ብሎ ማየት እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ወደ ጫካ በተገባበት ወቅት የነበሩት ምክንያቶች ህዝቡ በማንነቱ ይፈናቀላል፣ ይገደላል ያን ማስቆም አለብን እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው የሚሉ እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተጨባጭ ግን ባለፉት ዓመታት የታዩት ውጤቶች ከቀረቡት ዓላማዎች ጋር ፈጽሞ የሚቃረኑ ሆነው ተገኝተዋል ብለዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ውስጥ ሰው ከቤቱ ሲወጣ የሚሸማቀቅበት፣ በሰላም ለመመለሱ ምንም ዓይነት ዋስትና የሌለው፣ ሀብትና ንብረቱ የሚዘረፍበት፣ አዛውንቶችና ትላልቅ ሰዎች የሚገደሉበት እንዲሁም መምህራን የሚታገቱበት ከባድ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

በመሆኑም የአማራ ህዝብ ነገርን ከስሩና ከመሰረቱ ለማስተዋልና ለመገምገም የማይቸገር ብልህ ህዝብ በመሆኑ፣ የጉዳዩን መንስኤና ውጤት በጥልቀት ቢመለከተው የፍሬ ነገሩን እውነታ ለማግኘት እንደማይቸገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አብራርተዋል።

አክለውም ህዝቡ ይህንን በትግል ስም እየተፈጸመ ያለውን እውነታ በሚገባ ተረድቶ አካባቢውን ከጥፋት ሊታደግ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በይስሃቅ ታሪኩ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: