Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ክፍል አንድ ቆይታ ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች፡-

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 65

👉 ኢትዮጵያ ሕዝቦች በዘመናት መካከል አብረው ሲኖሩ በብዙ መልኩ የተጋመዱ፣ የተሳሰሩ፣ የተጋቡ፣ የተዋለዱ እና በጋራ የኖሩ ናቸው። 

👉 በተለይም አማራን እና ኦሮሞን ስንወስድ፣ በአቀማመጣቸው እና በቁጥራቸው ከፍ ስለሚሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መለስ ብለን እያንዳንዱን አንጓ ብንመዝን፣ በሦስት ዋና ዋና መንገዶች በስፋት የተጋመዱ መሆናቸውን እናያለን። እነዚህም ማኅበራዊ ጋብቻ፣ የፖለቲካ ጋብቻ እና ባህላዊው ጉዲፈቻ ናቸው። 

👉 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መለስ ብሎ የሚኮራበትን የዓድዋን ታሪክ ብናነሳ ምኒልክ ከገበየሁ ውጪ፣ ምኒልክ ከባልቻ ውጪ አልሠሩትም። በውኅደት የተሠራ የጋራ ድል ነው። በጋራ የተፋለምንበት፣ ለአንዲት ውድ እና የከበረች ሀገር ዋጋ ከፍለን ለማኖር ሀገራችንን እና የጋራ ኅልውናችንን አስቀድመን በጋራ ዘምተን፣ በጋራ ሞተን ያጸናናት ሀገር መሆኗን ያሳያል። 

👉 ከዚህኛው ለውጥ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ ለውጦች የአማራ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ እንዲመጣ፣ የፖለቲካ ሥርዓታችን እንዲሻሻል፣ የኢኮኖሚ ጉዟችን እንዲፋጠን እና ሕዝቦችን ያቀፈ እንዲሆን ትግል ሲያደርግ ነበር። 

👉 በ66ቱ፣ በ83ቱ እና በ2010ሩ ለውጦች ውስጥ የአማራ ሕዝብ ለውጥ መጥቶ ለመሻሻል እና ለማደግ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን ታሪክ ይናገራል።

👉 ከለውጥ ማግስት የነበረው ጉዞ የአማራ ሕዝብ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ተስፋ የተሞላበት፣ ሁለት እጁን ዘርግቶ ለውጡን የተቀበለበት እና ሀገር አፀናለሁ የሚል ህልም የታየበት ሁኔታ ነበረ። 

👉 ከ2010ሩ ለውጥ ቀደም ብሎ በነበረው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የመዘጋት፣ የመታፈን እና የመታሸግ ምልክቶች ነበሩ። 

👉 ፖለቲካችንም ኢኮኖሚውን ጭምር ታፍኖና ተዘግቶ ስለቆየ ከፈትፈት አድርጎ ማናፈስ ይፈልግ ነበር።

👉 በዚያ በነበረ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ ለውጡ እንደመጣ መስኮቶቻችንን ከፋፈትን። እነዚያ መስኮቶች ከእስር ቤት፣ ከውጭ ሀገር እንዲሁም የፖለቲካ ዝንባሌ የማይታይባቸው ሰዎች የፖለቲካ ስሜት እንዲላበሱ በማድረግ ብዙ አይነት ሰዎች በፖለቲካ አውድ ውስጥ ለመሳተፍ ሙከራ አድርገዋል። 

👉 ነገር ግን አንድ ሰው የተዘጋ ቤቱን ንፁህ አየር ለማስገባት መስኮት ሲከፍት ንፁህ አየር ብቻ አይደለም ወደ ቤቱ የሚገባው። አብረው ትንኞች እና ቢንቢዎች ይገባሉ። ቢንቢ በሳይዟ በጣም ትንሽ ብትሆንም ድምጿ እንዳትተኛ ታውካሃለች፣ ትቀሰቅስሃለች፤ ከዛም አልፎ በመንደፍ ደምህን ትጠጣለች፣ በሽታም ታመጣብሃለች። እንደዚህ ያለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ተፈጥሯል። 

👉 በማናፈሱ ውስጥ ተቀላቅለው የገቡ፣ ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት ለማወክ የሞከሩ፣ ከዛም ሲያልፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመናደፍ እና የኢትዮጵያን ኅልውና ለመገዳደር ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር እስከ መሰለፍ የሄዱ ዝንባሌዎች ታይተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: