Search

አረንጓዴ ዐሻራ፡- የግብርና፣ የቱሪዝም እና የታዳሽ ኃይል ስትራቴጂካዊ ትስስር

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 57

ኢትዮጵያ ወደ ከፍታዋ ለመድረስና የሕዝቧን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ከተፈጥሮ የተዋደደ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ የዕድገት አቅጣጫን መተግበር ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡

ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን ተቋቁማ በራሷ አቅም የዘመናችን ዓድዋ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን በማድረግ ለታዳሽ ኃይል አቅርቦት አይበገሬነቷን ለዓለም አሳይታለች፡፡

ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩና እየተገነቡ የሚገኙ ሌሎች የውሃ፣ የነፋስ እና የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችም ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለውን የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ አመላካች ናቸው፡፡

የዘርፉ ምሁራን እንደሚስማሙበት አረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ ቀጣይነት ያለው ዕድገት የሚረጋገጥበት ተግባራዊ እርምጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከቃል ባሻገር በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘው ሕዝብን ያሳተፈ አረንጓዴ አብዮት ወደ ኋላ የማይቀለበስ ፈጣን ዕድገቷ መሠረት እያፀና ይገኛል፡፡

ከለውጡ በፊት የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት "ግብርና መር" ይባል እንጂ ግብርናውም ጭምር ከዝናብ ጥገኝነት ሳይላቀቅ፣ ከሞፈርና ከቀንበር ተሻግሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ሳይዋሄድ ቆይቷል።

የደን ሀብቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱ ደግሞ ችግሮች “ከድጡ ወደ ማጡ” በመወሳሰባቸው ይተገበር የነበረው የልማት አቅጣጫም የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚችል አቅም እንዳልነበረው በተጨባጭ ታይቷል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ፕሮግራሞች ተግባራዊ ስለሆኑ፣ ትኩረት ተነፍጓቸው የቆዩ ዘርፎች ጭምር የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ቢኖሯትም ለውጭ ሀገር ዜጎች ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝባችንም በአግባቡ ሳይተዋወቁ በመቆየታቸው ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ሳታገኝ መቆየቷን ኢኮኖሚያዊ አሐዞች ይጠቁማሉ።

ከአምስቱ የብዝኃ ኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ፀጋዎችን በመግለጥ፣ መንገድን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ በማስቻል፣ የሕዝባችንን መስተጋብር በማሳደግ፣ የሀገራችንን መልካም ገፅታ በመገንባት ለሌሎች ዘርፎች ማንሰራራትም ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የማዕድን፣ የአይሲቲ እና የቱሪዝም ብዝኃ ኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ለአንዱ መስፈንጠር አቅም በሚፈጥር መልኩ እየተተገበሩ ሲሆን፣ አረንጓዴ ዐሻራን የመሳሰሉ ኢኒሼቲቮችም የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እያሳለጡ ይገኛሉ።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ከሚያበረክተው ከፍተኛ አስተዋፅዖ ባሻገር ለቱሪዝሙ ዘርፍ መነሳት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው መታየት ጀምሯል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መተግበር ከጀመረ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የወንዞቻችን አቅም ጎልብቷል። የሁሉም ዜጋ ታሪካዊ ዐሻራ ያረፈባቸው ታላላቅ ግድቦች በደለል ከመሞላት ተጠብቀዋል። የተራቆተው የሀገራችን ገፅታም “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል እና በሌሎችም መሪ ቃሎች በተከታታይ ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮች ልምላሜን እየተጎናፀፈ ይገኛል፡፡

አረንጓዴ ልማታችን ለቱሪዝም ዘርፉ ፅኑ መሠረት ሲሆኑ፣ እየለሙ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ደግሞ አረንጓዴ ልማታችን ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ጉልህ ሚና መጫዎታቸውን በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ የለሙ የትውልድ ዐሻራዎችን መመልከት በቂ ነው።

የብዝኃ ኢኮኖሚ የትኩረት መስኮች እርስ በእርስ ተሳስረው፣ አንዱ ለአንዱ አቅም ከመሆናቸው ባሻገር ለዘላቂ እድገት ፅኑ መሠረት በሆነው አረንጓዴ ልማት ምቹ መደላድል ተፈጥሮላቸዋል።

ከተፈጥሮ የተስማማውና ነገን ታሳቢ ያደረገው አረንጓዴ ልማታችን የምግብ ዋስትናን እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ብርቱ ርብርብም ተጨማሪ አቅም መፍጠር ችሏል።

በአንድ በኩል የአየር ንብረትን በማስተካከል ለምርታማነት ማደግ ትልቅ ድርሻ እያበረከተ ሲሆን፣ መርሐ ግብሩ ለምግብነት የሚያገለግሉ አቮካዶ፣ ቡና፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አፕል እና መሰል አትክልትና ፍራፍሬዎችን በብዛት እንዲያካትት የተቀየሰው ስትራቴጅካዊ ስልት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚቻልበትን አውድ እየፈጠረ ይገኛል።

በተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች እንዲሁም በበርካታ የውስጥ ተግዳሮቶች ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የ7 ነጥብ 5 በመቶ አማካይ ዕድገት በማስመዝገብ ለተግዳሮቶች የማይበገር ኢኮኖሚ እየገነባች እንደምትገኝ ለዓለም አሳይታለች።

የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋት በአንድ ጀምበር የሚታይ ሳይሆን፣ እያደር የሚፈካ የዘላቂ ዕድገታችን ካስማ ነው፡፡ በመላ ሀገራችን የተተከሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ቀጣይነት ላለው እድገት የሚኖራቸው አበርክቶ ላቅ ያለ በመሆኑ፣  እያደገ የመጣው ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ባህል ለሀገራችን ፈጣን እድገት ፋይዳው የጎላ ነው።

በብርሃኑ አምኃ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: