Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ክንፍ፤ የቢሾፍቱ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ

ቅዳሜ ሐምሌ 25, 2018 55

የአፍሪካ አቪዬሽን ዘውድ የደፋው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በየዓመቱ የሚያስመዘግበው አስደናቂ የገቢ ዕድገት፣ የደንበኞች ቁጥር መጨመር፣ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት እና የመዳረሻዎች መጨመር ተራ ስታቲስቲክስ ብቻ አይደለም።

ይህ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው አፈጻጸም ሀገራችንን የአህጉሪቱ ዋና የመሸጋገሪያ (Transit) ማዕከል ያደረጋት ሲሆን፣ አሁን ካለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅም በላይ የሚጠይቅ ግዙፍ እውነታን ፈጥሯል።

ይህንን ዕድገት ዘላቂ ለማድረግና ሀገራችንን በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ካሉት ታላላቅ ተወዳዳሪዎች ተራ ለማሰለፍ በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ግዙፍ የአቪዬሽን ማዕከል ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዓመቱ እያሳየ ያለው ከፍተኛ አፈጻጸም አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እንዲጀመር ቀጥተኛ ምክንያትና መሪ ኃይል ሆኗል።

በየዓመቱ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞችን እና በመቶ ሺህ ቶን የሚቆጠር ጭነት የሚያስተናግደው አየር መንገዱ፣ አሁን ያለው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የማስተናገድ አቅሙ በመጨመር በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ መጨናነቁ የማይቀር ነው።

በመሆኑም አየር መንገዱ የሚያዛቸው ዘመናዊ እና ግዙፍ አውሮፕላኖች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ሰፊ የማረፊያ፣ የጥገና እና የቴክኒክ ማዕከላት ያስፈልጋሉ።

የላቀ የአየር መንገድ አገልግሎት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ አየር መንገዱ እያሳየ ያለው ስኬት በዘመናዊ መሠረተ ልማት ካልተደገፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ማስቀጠል አዳጋች ይሆናል።

ለዚህም ሲባል በቢሾፍቱ  እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የአውሮፕላን ማረፊየ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ኢኮኖሚያዊ ገጽታ የሚቀይር ግዙፍ መሠረተ ልማት ነው፡

ኤርፖርቱ በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምር በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህም ከአፍሪካ ትልቁና በዓለም ደረጃም ከቀደሙት ተራ የሚሰለፍ ያደርገዋል።

ቢሾፍቱ ከባሕር ወለል በላይ ያላት ከፍታ አነስተኛ በመሆኑ፣ አውሮፕላኖች አነስተኛ ነዳጅ ተጠቅመው በሙሉ የጭነትና የመንገደኛ አቅማቸው እንዲበርሩ ያስችላቸዋል። ይህም ለአየር መንገዱ ከፍተኛ የወጪ ቆጣቢነትን ያመጣል።

አዲሱ ማዕከል በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የተደራጀ፣ ፈጣን የመሸጋገሪያ (Transit) ጊዜን የሚያረጋግጥ እና የመንገደኞችን እንግልት የሚቀንስም ይሆናል።

የአዲሱ አውሮፕላን መረፊያ መገንባት ከአቪዬሽን ዘርፍ አልፎ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ንቅናቄን ይፈጥራል። እንዲሁም ከአዲስ አበባ እና ከአካባቢው ከተሞች ጋር በፈጣን ባቡር፣ በከፍተኛ መንገድና በኤክስፕረስ ዌይ ይገናኛል። ይህም የመንገደኞችን እና የካርጎ እንቅስቃሴን ያቀላጥፋል።

አዲሱ የአቪዬሽን ማዕከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠሩ ባሻገር፣ ለአቪዬሽን ከተማ ፣ ለሆቴሎች፣ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም እና ለሎጂስቲክስ ኤክስፖርት ዘርፍ ግዙፍ መነቃቃትን ያመጣል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስመዘገበውና እያስመዘገበ ያለው ከፍተኛ አፈጻጸም፣ የቢሾፍቱው አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲወለድ መሠረት ሆኗል።

አዲሱ የአቪዬሽን ማዕከል አየር መንገዱ ለጀመረው የዕድገት ጉዞ በቂ የኦፕሬሽን ምህዳር በመፍጠር፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ካርታ ላይ ያላትን መሪነት የሚያጸና እና የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን የሚያፋጥን ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: