Search

ታሪካዊና መልክዓ ምድራዊ እውነታዎችን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት አቋም

ረቡዕ ሐምሌ 29, 2018 115

ለኢትዮጵያም ሆነ ለማንኛውም ሀገር የባሕር በር ማግኘት ከመሠረተ ልማት በላይ የሆነ የሁለንተናዊ ዕድገትና የኢኮኖሚ ልማት መስመር የሚወስን ታላቅ ሀገራዊ ሀብት ከመሆኑም በላይ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር የሚደረግን ሁለገብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ የሚያጎለብት ስትራቴጂካዊ መሠረት ነው።

በዓለም ላይ አብዛኛው ንግድ በባሕር መጓጓዣ ስለሚከናወን የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት አላቸው።

በተቃራኒው ኢትዮጵያ በታሪካዊ አጋጣሚዎችና በፖለቲካዊ ሴራዎች ምክንያት የባሕር በሯን እንድታጣ መደረጓ ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ወጪ፣ ለምርት ዋጋ መጨመር እና ለብሔራዊ ደህንነት ስጋቶች ዳርጓታል።

ይሁን እንጂ 130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የዕድገት ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ ይህንን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ፍትህ የማጣት ሁኔታ በዘላቂነት ተሸክማ መቀጠል አትችልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ኢትዮጵያ ተዘግታ እንደማትኖር ያነሱትን ሀሳብ ተከተሎ የመደመር መንግሥት ጉዳዩን የሀገራችን ዋና የጂኦፖለቲካዊና የህልውና አጀንዳ እንዲሆን አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ጥያቄ ከታሪካዊ እውነታዎች፣ ከመልክኣ ምድራዊ አቀማመጥ እና ከፍትሃዊ የንግድ መርሆዎች ጋር የተያያዘ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነቷን በሰላማዊ ውይይት፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በኢኮኖሚያዊ ትብብር እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ጥያቄዋን እያቀረበች ትገኛለች።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀ መከላከያ ሠራዊት በመገንባት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን በስኬት እየተወጣች በመሆኗ፣ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስፈን የበለጠ አቅም ይፈጥራል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ጥያቄ በመደገፍ አወንታዊ ሚና ሊጫወት እንደሚገባው የሚታመን ሲሆን፣ መላው ኢትዮያውያንም ይህ ቁልፍ የብሔራዊ ጥቅም እና የህልውና ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በአንድነት ሊቆሙ ይገባል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: