ጦርነት ለብዙኃኑ ንጹሐን ዜጎች ሞት፣ ስደት እና ውድመት ሲሆን፣ ለአንዳንዶች ግን እጅግ አዋጭ የሆነ የንግድ ዘርፍ ነው።
አሜሪካዊው ጄኔራል እና ጸሐፊ ስሜድሊ በትለር በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት በሚታወቀው "War is a Racket" (ጦርነት የጥቅም ማጋበሻ ቁማር ነው) በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፉ ይህንን መራራ እውነታ አፍረጥርጦ አቅርቦታል።
በትለር በመጽሐፉ እንደሚያብራራው፣ ጦርነት ማለት ጥቂት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ልሂቃን የደሃውን ልጅ ደም እያፈሰሱ የራሳቸውን የባንክ አካውንት የሚያደልቡበት፣ የጥይት ፋብሪካዎች እና የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎች የሰውን ደም እየጠጡ የሚያብቡበት ክፉ የንግድ ሥርዓት ነው።
በተመሳሳይ የፖለቲካ ምሁሩ ዴቪድ ኪን "The Economic Functions of Violence in Civil Wars" በሚለው ጽሑፉ እንዳረጋገጠው፣ ልክ በድህነት ላይ እንደሚነግዱት ‘Lords of Poverty' ሁሉ፣ በጦርነትም ውስጥ የሰውን ሕይወት የሚገበያዩ "የግጭት ጌቶች" አሉ።
እነዚህ ኃይሎች ከቀውስ፣ ከግጭት እና ከደም መፋሰስ ውስጥ ጥቅም እንዴት እንደሚገኝ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ጥይት በመሸጥ፣ ሕገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ በማስፋፋት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታን በመመዝበር እና ሀገርን በማተራመስ የራሳቸውን የሀብት ቋት ይሞላሉ።
ለእነዚህ አካላት ሰላም ሲመጣ ዋነኛ ንግዳቸው ስለሚከስር፣ ሁልጊዜም ማኅበረሰቡን በስጋት እና በግጭት ውስጥ ማቆየት ዋነኛ የሕልውናቸው መሠረት ነው።
ይህን ዓለም አቀፍ የጦርነት ንግድ ስሌት እና ጽንሰ ሐሳብ ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስናመጣው፣ የከሰረው የህወሓት ቡድን ትክክለኛ ማንነት ፍንትው ብሎ ይታየናል።
ይህ የጥፋት ቡድን ገና ከመነሻው፣ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ሕገ ወጥ ባሕርይ የተላበሰ፣ በተለያዩ የሕገ ወጥነት ተግባራት ላይ የተሰማራ እና እኩይ ተፈጥሮ ያለው ቡድን ነው።
የተረጋጋች ሀገር፣ የተስማማ ሕዝብ፣ የሕዝቦች ጠንካራ አንድነት እና ሀገርን የማዳን አስተሳሰብ ፈጽሞ የማይዋጥለት ቡድን ነው። ለምን ቢባል? ምክንያቱም የቡድኑ የሕልውና መሠረት እና የትርፍ ማግበስበሻ ስሌቱ ያለው በግጭት ውስጥ በመሆኑ ነው።
የከሰረው የህወሓት ቡድን ገና ከንጋቱ ጀምሮ የትግራይን ሕዝብ ሆን ብሎ በቋሚ የጦርነት ሥነልቦና ውስጥ አስገብቶ በማቆየት፣ የራሱን ግዙፍ የቤተሰብ እና የልሂቃን ቢዝነስ ኢምፓየር ሲገነባ ኖሯል።
"የትግራይ ሕዝብ በጠላቶች ተከብቧል" የሚል የውሸት ትርክት በመፍጠር እና ወጣቱን ወደ ጦርነት እሳት በመማገድ፣ የቡድኑ መሪዎች በደም በተጨማለቀ ገንዘብ የጥቅም ትሥሥራቸውን አደልበዋል። በመንግሥት ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመንም ሆነ አሁን በትጥቅ ትግል ስም፣ ዋነኛ ዓላማቸው ቀውስን መነገድ ነው።
የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን በጦር ሜዳ ሲቀብሩ፣ የቡድኑ መሪዎች ግን በልጆቹ ደም አዳዲስ የንግድ ተቋማትን፣ የኮንትሮባንድ መስመሮችን እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መረቦችን በሀገር ውስጥም በውጭም ዘርግተዋል።
በመሆኑም፣ ዛሬም ቢሆን የጦርነት ነጋሪት ሲጎስሙ የሚሰሙት ለሕዝብ አስበው ወይም ለትግራይ ሕዝብ መብት ተቆርቁረው አይደለም። ግጭት ለእነሱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው፤ ጥይት የዕለት ተዕለት ሸቀጣቸው ነው፤ የሰው ሕይወት ደግሞ የፖለቲካ ትርፍ ማግበስበሻ የሚከፈል ዋጋ ነው።
የትግራይን ወጣት ከማይመለከተው እና ከማያተርፍበት የጥፋት ጦርነት ውስጥ ደጋግሞ በመማገድ የከሰረው የህወሓት ቡድን “የግጭት ጌቶች” የቤተሰብ ኢምፓየራቸውን ለማስቀጠል አሁንም እየታገሉ ይገኛሉ።
ታዋቂው የታሪክ ምሁር ሄሮዶተስ የጦርነትን አስከፊነት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ "በሰላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤ በጦርነት ጊዜ ግን አባቶች ልጆቻቸውን ይቀብራሉ።" ይህ ጥልቅ የሕይወት ፍልስፍና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የጦርነት ነጋሪት ለሚጎስሙት በሙሉ የተነገረ ቁልጭ ያለ እውነት ይመስላል።
እንደወጉ ለሰላም እንትጋ እና ልጆቻችን ይቅበሩን፤ አለዚያ በገዛ እጃችን ልጆቻችንን ወደ መቃብር እናወርዳለን። ከመቐለ እስከ ካይሮ፣ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ለተናበቡብን እና አሁንም በመናበብ ላይ ላሉት የጥፋት ኃይሎች በልካቸው የተሰፋ እውነት ነው።
ነገር ግን ይህ የጥፋት ነጋዴ የደም ንግድ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይቆማል። የትግራይ ሕዝብ ነቅቷል። የትግራይ ሕዝብ የዚህን እኩይ ስብስብ ማንነት እና ባሕርይ በሚገባ ካወቀ ከራርሟል። ይህንን የሞት ነጋዴዎች ቡድን ወጣቱ እርግፍ አድርጎ በመተው ራሱን ከትርፍ ማጋበሻነት በማላቀቅ እያሸሸ እና ራሱን እያስመለጠ ይገኛል።
በግጭት ነጋዴዎች የትርፍ ስሌት ልጆቹን እንዲቀብር የሚፈልጉትን የጥፋት ነጋዴዎች ሴራ በጥበብ በመበጠስ፣ ልጆቹን በእርጅና ዘመን በክብር የሚቀብሩበትን ጽኑ የሰላም ዘመን መገንባት ታሪካዊ ግዴታዬ ነው ብሎ ተነሥቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: