አንዲት ሀገር እውነተኛ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ ሉዓላዊነቷን በተግባር የምታረጋግጠው በምግብ፣ በቴክኖሎጂ እና በውጊያ ቁሳቁሶቿ የሌሎችን ደጅ ማየቷን ሙሉ በሙሉ ስታቆም ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች እና ወታደራዊ ቁሳቁሶች ላይ የተንጠለጠለችበትን የታሪክ አዙሪት በጥበብ እና በቆራጥነት እየሰበረችው ትገኛለች።
ዛሬ ላይ በወሳኝ ክፍለ ኢኮኖሚዎች እና በመከላከያ ዘርፍ በገዛ አቅሟ ራሷን ለመቻል አዲስ ታሪካዊና መዋቅራዊ ምዕራፍ ከፍታለች።
የሀገራችን የመከላከያ ኢንዱስትሪ አሁን ላይ የሀገራዊ ቴክኖሎጂ እና የምህንድስና ማዕከል በመሆን፣ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ከመሥራት አልፎ አጠቃላይ የሀገራችንን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅስ የማይበገር ሞተር ሆኖ ተቀርጿል።
በመንግሥት የተቀረጹት ጥልቅ የመዋቅር ማሻሻያዎች እና "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ያመጡት ተጨባጭ ውጤት የዚህ ታላቅ ጉዞ ህያው ማረጋገጫ ነው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ተነስቶ ወደ 66.3 በመቶ ከፍ ማለቱ፣ እንዲሁም ዘርፉ ዓመታዊ የ10.7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ ሀገራችን ወደ አምራችነት በጽኑ መሸጋገሯን ያሳያል።
ከዚህም ባሻገር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 4.85 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ ኢትዮጵያ ከአስመጪነት ጥገኝነት ለመላቀቅ ያላትን ጽኑ አቋም በቁጥር የሚያረጋግጥ ነው።
በተለይም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገቡ የነበሩ እንደ የመከላከያ ሠራዊት አልባሳት ያሉ ቁሳቁሶች አሁን ላይ 100 በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት መተካታቸው የኢትዮጵያን አቅም በተግባር ያሳዩ አብነቶች ናቸው።
ይህ ስኬት የተጠና ራዕይ ውጤት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚያስምሩበት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች ሚና ድንበር ከመጠበቅ የሚዘል ነው።
እውነተኛ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው ትጥቅን በራስ አቅም በማምረት በመሆኑ የመከላከያ ተቋማቶቻችን ሀገራዊ የኢንዱስትሪ አብዮትን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የማፋጠን ታላቅ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት እና የፈጠራ አቅም ማሳደግ ወታደራዊ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አድርጓል።
ከዚህም ባለፈ ለሲቪል ኢኮኖሚው ጭምር የሚጠቅሙ ባለሁለት ጎን (Dual-use) ቴክኖሎጂዎችን ለማፍራት የሚያስችል የማይናጋ መሠረት ጥሏል። በመከላከያ ዘርፍ የተመዘገበው የወታደራዊ እና የቴክኖሎጂ ዘመናዊነት በተግባር የሚታየውም በዚህ ልክ ነው።
አሁን ላይ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎቻችን በጋፋት አርማመንት በኩል ዘመናዊ ቀላል እና ከባድ አውቶማቲክ የጦር መሣሪያዎችን ማምረት ችለዋል። በሆሚቾ አሙኒሽን በኩል ጥይቶችን እና ከባድ መድፎችን፣ እንዲሁም በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በኩል የላቀ ጥንካሬ ያላቸውን የታጠቁ የውጊያ እና የሰው ማጓጓዣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን (APCs) እና ታንኮችን በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማምረትና በማደስ ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በደጀን አቪዬሽን ኢንጂነሪንግ በኩል የጦር ጄቶችን እና ሄሊኮፕተሮችን ሙሉ ጥገና እና ማሻሻያ ከማድረግ አልፈው ዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂዎችን እና የራዳር ሥርዓቶችን የመገንባት አቅም ላይ ተደርሷል።
ይህ ስኬት የመከላከያ ሠራዊታችንን በቀጣናው ግዙፍ እና የማይበገር የቴክኖሎጂ ባለቤት አድርጎታል። ይህ ስትራቴጂካዊ አቅም ኢትዮጵያ ለጦር መሣሪያ ግዢ ታወጣ የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማዳን ሀብቱን ለሌሎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶች እንድታውል እያስቻላት ይገኛል።
የኢትዮጵያ የምርት መተካት እና የመከላከያ መዘመን ጉዞ የሀገራዊ ሉዓላዊነት፣ የጽናት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ህያው መግለጫ ነው።
የመከላከያ ኢንዱስትሪዎችን ከሲቪል ኢንዱስትሪዎች ጋር በማጣመር የተገነባው ይህ የተቀናጀ ሀገራዊ ቁመና ኢትዮጵያን በማንኛውም ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና የማትበገር፣ የራሷን ዕድል በራሷ የምትወስን እና የአፍሪካ አህጉር ኩራት አድርጎ እየገነባት ይገኛል።
ይህ ታሪካዊ ሽግግር የነገዋን ራሷን የቻለች፣ የታጠቀች፣ የበለጸገች እና በምንም ዓይነት መዋቅራዊ ጥገኝነት ውስጥ የማትወድቅ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ የተጣለ የማይናጋ የነፃነት መሠረት ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: