የግብፅ የውኃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስትር ሃኒ ሴዊላም ሰሞኑን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ተጨማሪ ግድቦችን እንድትገነባ ካይሮ "አትፈቅድም" በማለት ያሰሙት ዛቻ፣ በቀጣናው ሃይድሮ-ፖለቲካ ውስጥ የቆየውን የነጠላ ፍላጎት የበላይነት የመጫን አባዜ በድጋሚ የሚያንፀባርቅ ነው።
ነገር ግን ይህ የካይሮ ዛቻ ከተፈጥሯዊ፣ ሃይድሮሎጂካል እና ዓለም አቀፍ የሕግ እውነታዎች ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ እና ውኃ የማያነሳ ሙግት ነው።
ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓባይ ውኃ የምታመነጭ፣ የሀብቱ ዋና ባለቤት እና ምንጭ ናት። በመሆኑም የገዛ ተፈጥሯዊ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷ በማንኛውም የውጭ ሀገር ፈቃድ፣ ይሁንታ ወይም እገዳ ስር የሚወድቅ አይደለም።
ከዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ውኃዎች ሕግ አንጻር ሲመዘን የግብፅ አቋም ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለውም። በ1997ቱ የተመድ የድንበር ተሻጋሪ ውኃዎች ኮንቬንሽን እና በተለመዱ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች መሠረት፣ የወንዝ ተፋሰስ ሀገራት መብት በሚመራበት ዋናው መርህ "ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም" ላይ የተመሰረተ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ መቼም ቢሆን አቋሟ ሌሎችን መጉዳት ሳይሆን ሁሉም የሚያተርፍበትን ፍትሐዊ አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ ነው።
በተለይም በቅርቡ በቂ የሀገራት ፊርማ አግኝቶ ወደ ትግበራ የገባው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ እና ኢትዮጵያን ያላካተቱ ስምምነቶችን ጠቅሳ "ታሪካዊ መብት አለኝ" የምትለውን ራስ ወዳድ ሙግት ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ ሕግ ውድቅ ያደረገው ነው።
የላይኛው ተፋሰስ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ውኃውን ለኃይል ማመንጫነት ማዋሏ በዓለም አቀፍ ሕግ የተቀመጠውን ፍትሐዊ የመጠቀም መብት የሚያረጋግጥ እንጂ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ "ጎልቶ የሚታይ ጉዳት" የሚያስከትል አለመሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬታማ ግንባታ እና የውኃ ሙሌት በተግባር አረጋግጦታል።
በዓለም አቀፍ የሀገራት ልምድም ቢሆን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የራሳቸውን ወንዞች ለማልማት ከታችኞቹ ሀገራት ፈቃድ የሚጠይቁበት አሠራር የለም። ለምሳሌ አሜሪካን ብንመለከት፣ ከሜክሲኮ ጋር በምትጋራቸው የኮሎራዶ እና ሪዮ ግራንዴ ወንዞች ላይ ግዙፍ ግድቦችን እና የውኃ ማዞሪያ ፕሮጀክቶችን ስትገነባ፣ የራሷን የልማት እና የኃይል ፍላጎት መሠረት በማድረግ በሉዓላዊነቷ ነው። ታችኛው ተፋሰስ ላይ ያለችው ሜክሲኮ በአሜሪካ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የመከልከል መብት ኖሯት አያውቅም።
በተመሳሳይ መልኩ ቱርክዬ በኤፍራጥስ እና ጢግሮስ ወንዞች ላይ ተግባራዊ ያደረገችውን ታላቁን የደቡብ ምሥራቅ አናቶሊያ ፕሮጀክት ስታካሂድ፣ አታቱርክን ጨምሮ በርካታ ግድቦችን የገነባችው የራሷን ሕዝብ ሕይወት ለመቀየር ባላት ሉዓላዊ መብት ነው።
ቱርክዬ የወንዞቹ ዋና ምንጭ በመሆኗ እንደ ኢራቅ እና ሶሪያ ባሉት የታችኞቹ ሀገራት የሚቀርቡትን የወንዙን ፍሰት ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ወይም የመከልከል ጥያቄዎች ውድቅ በማድረግ፣ ፍትሐዊ አጠቃቀምን መሠረት ያደረገ የልማት መስመር ተከትላለች።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታካሂዳቸው ማንኛቸውም ፕሮጀክቶች በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ሕይወት የመቀየር፣ ድህነትን የመዋጋት እና ኢኮኖሚዋን የማሳደግ ፍጹም እና ተፈጥሯዊ መብቷ ውጤቶች ናቸው።
ሆኖም ኢትዮጵያ ይህን መብቷን ስትጠቀም የራስ ወዳድነት አቋም አትከተልም። ይልቁንም ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና መርሆዎችን ባከበረ፣ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት ባገናዘበ እና በጋራ ልማት ላይ በተመሰረተ መንገድ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን እ.አ.አ በ2015ቱ የመሪዎች መርሆዎች ስምምነት (DoP) እና በተግባራዊ እንቅስቃሴዎቿ አስመስክራለች። የሕዝቦቿን ኑሮ የመቀየር መብቷን ሳታስደፍር ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በትብብር የመልማት አቅጣጫን በጽናት ትከተላለች።
ስለሆነም የግብፅ ኃላፊዎች የሚያሰሙት "አንፈቅድም" የሚል ዛቻ፣ የዓባይን ተፈጥሯዊ ምንጭ እና የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ የሚያስቆም ሳይሆን፣ የቀደመውን ራስ ወዳድ እና አግላይ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ብቻ ነው።
በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችለው፣ ግብፅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት እና የ85 በመቶ ውኃ ምንጭነት አምና በመቀበል በፍትሐዊነት እና በትብብር መርህ ላይ የተመሰረተ አቅጣጫ ስትከተል ብቻ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: