ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ነገ ነሐሴ 1 ቀን የሚጀመረውን የ2018 ዓ.ም የጾመ ፍልሰታ ሱባኤን አስመልክተው ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ እግዚአብሔርን መውደድ በተግባር የሚገለጸው ትእዛዙን በመጠበቅና የሰው ልጅን በሙሉ እንደ ራስ አድርጎ በመውደድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ለ15 ቀናት የሚጾመው የጾመ ማርያም (ፍልሰታ) መነሻ ምክንያትም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ እና ፍቅር መሆኑን በመጠቆም፣ አምላክ የመረጣትን እና ከፍጥረታት ሁሉ አልቆ ያከበራትን ድንግል ማርያምን ማክበር አምላካዊ ትዕዛዝን መጠበቅ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም ምዕመናን ይህንን የሱባኤ ወቅት የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የታመሙትን እና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ እንዲሁም ለኃጢአት የንስሐ ሥርየትን በመለመን እና ቅዱስ ቁርባን በመቀበል ሊያሳልፉት እንደሚገባ አባታዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በሀገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ስጋት የሆነውን የፍጥረት አውዳሚ ጦርነት እግዚአብሔር በመለኮታዊ ጥበቡ እና ሥልጣኑ እንዲያስቆም፣ ምዕመናን በቅን ልቦና እና በትሑት ሰብእና ሆነው በሱባኤያቸው በጸሎት እንዲጠይቁ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አደራ ብለዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: