ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ግዙፍ የሆነውን የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባሕር ዳር የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም እና የዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ማዕከልነቷ ይበልጥ እየጎላ መምጣቱን ገልጸዋል።
አዲሱ ተርሚናል በከተማዋ ለተከናወኑት እና እየተከናወኑ ላሉት ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ትልቅ የኢኮኖሚ እና የንግድ እንቅስቃሴ ብሥራት እንደሚሆን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከተማዋ ከቱሪዝም አቅሟ በተጨማሪ በኢንዱስትሪው መስክ ያላትን ከፍተኛ አቅም ለመጠቀም የኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነባባት፣ በምሳሌነት የሚጠቀሱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለቤት እንዲሁም በግዝፈቱ እና በጥራቱ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ድልድይ የተገነባባት ከተማ መሆኗን አብራርተዋል።
በከፍተኛ ጥራት የተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማዋን ውበት ይበልጥ በማሳደግ የሀብት እና የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል የሚያደርጋት ከመሆኑም በላይ ለቱሪዝም ያላትን ተመራጭነት ያጎላዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
በከተማዋ እየተገነባ የሚገኘው ስታዲየም ሲጠናቀቅ ከሀገር ውስጥ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ በርካታ እንግዶችን አስተናጋጅ በመሆን የከተማዋን ውበት፣ ታሪክ እና መልካም ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቅ እንደሚሆን አብራርተዋል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: