ታዋቂው የህንድ ሚዲያ ተቋም የሆነው 'ፈርስት ፖስት' በቅርቡ ስለ ኢትዮጵያ ባሰራጨው ወደ ዘጠኝ ደቂቃ በሚጠጋ ጥልቅ ትንታኔው ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት አስደናቂ የኢኮኖሚ ሽግግር እያደረገች መሆኗን ዘግቧል።
ሚዲያው በዘገባው እንዳስገነዘበው፣ ለረጅም ዓመታት በጦርነትና በድርቅ ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ላይ ይህንን የተዛባ ትርክት በመቀየር በኢነርጂ፣ በአቪዬሽን፣ በማዕድን እና በዲጂታል ኢኮኖሚ መስኮች የአፍሪካ ኃያል ሀገር ለመሆን በተግባር እየሰራች ትገኛለች።
እንደ 'ፈርስት ፖስት' ዘገባ ከሆነ፣ ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ሽግግር ዋነኛ ሞተር የሆነው ከ5 ሺህ ሜጋዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው።
ይህ ግድብ ከየትኛውም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ብድር ሳይወሰድበት በኢትዮጵያውያን የገንዘብ፣ የላብና የደም አስተዋጽኦ ብቻ መገንባቱ፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን ህልም ማሳካት እንደሚችሉ ያረጋገጠ ትልቅ ራስን የመቻል ማሳያ መሆኑን ሚዲያው አብራርቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክን ለጎረቤት ሀገራት በማቅረብ የቀጣናው የትስስር ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ተቋሙ አድንቋል።
በአቪዬሽኑ ዘርፍም ቢሆን በ12.5 ቢሊዮን ዶላር እየተገነባ ያለው አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን ተጓዦችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህም አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ የንግድና የቱሪዝም ዋነኛ መገናኛ እንደሚያደርጋት 'ፈርስት ፖስት' አትቷል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የወጪ ንግዱን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ ያለው የማዕድን ዘርፍ እና በሶማሌ ክልል እየተገነባ ያለው ግዙፉ የማዳበሪያ ፋብሪካ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ዘገባው አካቷል።
'ፈርስት ፖስት' በዘገባው እንደጠቀሰው፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በኢንቨስትመንት ማሻሻያዎች ረገድ ኢትዮጵያ አስደማሚ ለውጦችን እያሳየች ነው።
የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ስኬት፣ የቴሌኮም እና የባንክ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መሆን፣ እንዲሁም የካፒታል ገበያ መጀመር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚያሳድገው ተጠቅሷል።
የብሪክስ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ጎራ ሳትለይ ከሁሉም ጋር በመተባበር እያካሄደች ያለው ግዙፍ የኢኮኖሚ ሽግግር፣ በቀጣዮቹ ዓመታት የቀጣናውንና የአፍሪካን ገጽታ በአዲስ መልኩ የሚቀርጽ መሆኑን የህንዱ ሚዲያ 'ፈርስት ፖስት' ለዓለም ዘግቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: