ብልፅግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያገኘውን የህዝብ ውክልና ወደ ተጨባጭ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ለመቀየር በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራ አስታወቀ።
የፓርቲው የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ ጠንካራ ሀገር ለመገንባትና ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት ራዕይ ያለውና የተደራጀ ፓርቲ መገንባት ዋነኛ መነሻ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከህዝቡ ጋር የፈጠረው ጠንካራ ቁርኝት ለተመዘገቡት ስኬቶች መሰረት መሆኑንም አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት በፓርቲው መሪነት የተተገበሩት ስትራቴጂዎች ህዝባዊ ተቀባይነትን በማግኘታቸው ተጨባጭ ለውጦች መጥተዋል።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ በተደረጉ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ስኬታማ ጉዞ የጀመረች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቅ የስንዴ አምራች ሀገር መሆን ችላለች።
በሌላ በኩል በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም የተገነባ ሲሆን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የተከናወኑት የኮሪደርና የከተማ ልማት ስራዎች የሀገሪቱን ገጽታ በእጅጉ የቀየሩ ተግባራት ናቸው።
ፓርቲው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገባቸውን የማኒፌስቶ ሃሳቦች አሁን ላይ ወደ ዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብሮች እየቀየረ ይገኛል። በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ግብርናን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ቱሪዝምን፣ ማዕድንና ዲጂታል ኢኮኖሚን በማስፋፋት ሀገራችን ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማሸጋገር በርትቶ ይሰራል።
በተጨማሪም የማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት እንዲሁም በትምህርት፣ በጤና እና በቋንቋ ዕድገት ላይ በማተኮር ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል።
ከሁሉም በላይ የህዝቦችን አንድነት እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አሁን ላይ 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉበት የሚገኘው አካታች ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ፓርቲው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ኃላፊው አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: