Search

ዶ/ር መቅደስ ዳባ በባሕርዳር ከተማ የአረጋውያንን ቤትና የትምህርት ቤት ግንባታ አስጀመሩ

ዓርብ ነሐሴ 01, 2018 90

የጤና ሚኒስቴር በባሕርዳር ከተማ የአምስት አረጋውያንን የመኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲሁም የአንድ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታን በይፋ አስጀመረ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በባሕርዳር ከተማ ቁልቋል ሜዳ ትምህርት ቤት በመገኘት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ክፍል ግንባታ መሠረት ድንጋይ ያሰቀመጡ ሲሆን፤ በዚሁ መርሃ-ግብር ለ500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ድሃ ተኮር ተግባራት የላቀ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ በዘንድሮው መርሃ-ግብር ከህክምና መሳሪያዎች ጥገና ጀምሮ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉና ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበላቸው ስራዎች በመላ ሀገሪቱ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም በባሕርዳር ከተማ የተደረገው ድጋፍ የትምህርት ተቋማትን ከማጠናከርና የወላጆችን የኢኮኖሚ ጫና ከመቀነስ ባለፈ፣ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩና በዜጎች ዘንድ ባለቤትነት ስሜት እንዲጎለብት የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም በጤናው ዘርፍ በመላ ሀገሪቱ ለ20 ሚሊዮን ዜጎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉን አብራርተዋል።

በዕለቱ የተገኙት የባሕርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በበኩላቸው፣ በከተማዋ በ17 ዘርፎች ላይ ያተኮረ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በስፋት እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የጤና ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቶችና አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

 በራሄል ፍሬው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: