ታዋቂው የህንድ ሚዲያ 'ፈርስት ፖስት' (Firstpost) ኢትዮጵያ ከጦርነት እና ድርቅ ትርክት ወጥታ የአፍሪካ ቀንድን የኢኮኖሚ ካርታ ለመቀየር እያደረገች ያለውን ግዙፍ ሽግግር በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ዳስሶታል፦
• ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፦ ከ5,000 ሜጋዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው፣ ከዓለም ባንክም ሆነ ከአይኤምኤፍ (IMF) ምንም አይነት ብድር ሳይወሰድ በኢትዮጵያውያን አቅም ብቻ የተገነባ የኢኮኖሚ ነፃነት ሐውልት መሆኑን፤ እንዲሁም ለኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ኃይል በማቅረብ ቀጠናውን እያስተሳሰረ መሆኑን ዘግቧል።
• አዲሱ የቢሾፍቱ ሜጋ ኤርፖርት፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ12.5 ቢሊዮን ዶላር እየገነባ ያለው ይህ ኤርፖርት ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው እና አዲስ አበባን ዋነኛ የአፍሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ ማስተሳሰሪያ በር እንደሚያደርጋት አብራርቷል።
• የማዕድን ዘርፍ አብዮት፦ እንደ "ኩርሙክ ወርቅ" ያሉ ግዙፍ የማዕድን ፕሮጀክቶች አዳዲስ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን ለረጅም ጊዜ በግብርና ላይ ብቻ ጥገኛ የነበረውን ኢኮኖሚ እያዘመኑት መሆኑን ጠቅሷል።
• ግብርና እና የምግብ ዋስትና፦ አፍሪካዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ በሶማሌ ክልል የሚያስገነባው የ2.5 ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካ (በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን ምርት የሚሰጥ) የውጭ ጥገኝነትን በመቀነስ የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና እንደሚያረጋግጥ አትቷል።
• ዲጂታል ኢኮኖሚ እና የግል ዘርፍ ተሳትፎ፦ የ5G እና 4G ኔትወርኮች መስፋፋት፣ የዲጂታል ክህሎት ስልጠናዎች እንዲሁም ለበርካታ አሥርት ዓመታት ዝግ የነበሩት እንደ ቴሌኮም፣ ባንክ እና የካፒታል ገበያ (Securities Exchange) ለግል ኢንቨስትመንት ክፍት መደረጋቸውን በአድናቆት አንስቷል።
• የተሳካ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን፦ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል ሆና ሳለችም፣ ከዓለም ባንክ፣ አይኤምኤፍ፣ ቻይና፣ አረብ ሀገራት እና ምዕራባውያን ጋር ሚዛኑን የጠበቀ የኢንቨስትመንት ግንኙነት እያደረገች መሆኑን አስነብቧል።
የዋጋ ግሽበት፣ የዕዳ ጫና እና ቀጠናዊ የፀጥታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ግዙፍ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በተሳካ ሁኔታ የአፍሪካ ቀንድን የኢኮኖሚ ካርታ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሊቀይረው እንደሚችል ሚዲያው አስምሮበታል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: