Search

ከሕዳሴው ግድብ አራት እጥፍ የሚያመነጨው የኢትዮጵያ አዲሱ ግዙፍ የኃይል አብዮት

ዓርብ ነሐሴ 01, 2018 157

ዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ውድድር አዲስ ምዕራፍ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት፣ አስሩ የብሪክስ አባል ሀገራት ከዓለም አቀፉ የፀሐይ ኃይል ምርት 51 በመቶ የሚሆነውን በመሸፈን ግንባር ቀደም መሪዎች ሆነው ወጥተዋል። 

የዚህ ታሪካዊ ስኬት አካል የሆነችው ኢትዮጵያ ደግሞ ከትንሽ የኃይል ማመንጨት አቅም ተነስታ ወደ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ማኑፋክቸሪንግ የተሸጋገረችበትን አስደናቂ ታሪክ እያስመዘገበች ትገኛለች። 

ቻይና፣ ሕንድ እና ብራዚልን የመሳሰሉ የብሪክስ አባላት የዓለምን የንጹህ ኃይል ዕድገት 70 በመቶ እየሸፈኑ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፣ ኢትዮጵያ በ2024 ዓ.ም የምርት መጠኗን ከማሳደግም ባለፈ የፀሐይ ቴክኖሎጂ መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት ላይ ያተኮረ ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ ሽግግር አድርጋለች።

ለዚህም ማሳያ በሐዋሳ፣ በደብረ ብርሃን እና በአዲስ አበባ የተገነቡ ሥድስት ዘመናዊ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው ሲሆን፣ ሀገራችን በአንድ ዓመት ውስጥ ከምንም ተነስታ ግዙፍ የሶላር ሴል ማምረት ችላለች። 

እነዚህ ፋብሪካዎች በዓመት 20 ነጥብ 3 ጊጋዋት የፀሐይ ኃይል ሴል የማምረት አቅም ያላቸው ሲሆን፣ ይህም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን አጠቃላይ የማመንጨት አቅም በአራት እጥፍ የሚበልጥ ነው።

ይህ አስደናቂ የቴክኖሎጂ ሽግግር ቀደም ሲል ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ይገኝ የነበረውን ገቢ በእጅጉ በመብለጥ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ፣ 15 ሚሊዮን አባወራዎችን በኤሌክትሪክ ማብራት የሚያስችል ግዙፍ አቅም ፈጥሯል። 

ከዚህም ባሻገር የሀገር ውስጥ የሊቲየም ሀብትን ለባትሪ ምርት በማዋል፣ ኢትዮጵያ በኃይል ቴክኖሎጂ መቶ በመቶ ራሷን እንድትችል እና የምስራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል እንድትሆን ያደርጋታል። 

የብሪክስ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል መሪነታቸውን እያረጋገጡ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ማኑፋክቸሪንግ እመርታ የታዳሽ ኃይል አብዮት አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱን በጉልህ ያሳያል።

በሰለሞን ገዳ 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: