Search

የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ፡-የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ እስከ ሀገራዊ አንድነትና የኢኮኖሚ እመርታ

ዓርብ ነሐሴ 01, 2018 94

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ለደቀኗቸው ተግዳሮቶች ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ሆኗል።

በዚህ ረገድ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያሳተፈ ታላቅ ሀገራዊ ስኬት ማስመዝገብ ችሏል።

በዘመቻው “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል የተያዘውን ግብ በማለፍ 805.3 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ይህም ሀገራችን የራሷን ክብረ ወሰን በድጋሚ በማሻሻል ለተቀረው ዓለም አዲስ የተፈጥሮ ጥበቃ አርአያነት እንድታሳይ አድርጓታል።

ንቅናቄው የተራቆተ መሬትን በማንሰራራት፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የከርሰ ምድር ውሃን በማበልጸግ እና የደን ሽፋንን በማሳደግ በኩል የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ይህ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ ከሆነው የግብርና ዘርፍ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። በየዓመቱ የሚተከሉት የአቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ እና የዜጎችን የገቢ ምንጭ ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። በተጨማሪም ለሌማት ትሩፋት እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስኬት ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

ከአካባቢ ጥበቃና ከኢኮኖሚ ባሻገር፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ እንደ ዓድዋ ድል፣ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የሌማት ትሩፋት እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሁሉ ኢትዮጵያውያን በመደመር ዕሳቤ ሲተባበሩ የሚፈጥሩትን ታላቅ አቅም ለአፍሪካና ለዓለም ያረጋገጠበት አዲስ ምዕራፍ ነው።

የችግኝ ጉድጓድ አብሮ የመቆፈርና የመትከል ሂደት የዜጎችን ማህበራዊ መስተጋብርና ሀገራዊ አንድነት በማጠናከር "ከእኔነት ይልቅ የእኛ" የሚል የባለቤትነት ስሜት አጎልብቷል።

በአጠቃላይ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሥነ ምህዳርን ከመጠበቅ ባሻገር ተስፋን፣ የሀገር ፍቅርን እና ለአዲሱ ትውልድ ዘላቂ ሀብት የማውረስ ዕሴትን በማጠናከር ኢትዮጵያ የምትናገረውን የምትፈጽም ሀገር መሆኗን በተግባር ያስመሰከረ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: