Search

የ“ትዕግሥተኛዋ” ትዕግሥት አሰፋ የጽናት እና የድል መንገድ

እሑድ መስከረም 17, 2019 113

አንዳንድ ሰሞናት አሉ፤ ማለፊያቸው የሚናፈቅ። አንዳንድ ቀናት አሉ፤ ጀምበር አዘቅዝቃ ወደ ማደሪያዋ በመከተቷ እፎይታ የሚሆንበት። ንጋት ሩቅ የምትሆንባቸው አንዳንድ ሌሊቶችም አሉ። ሕይወት ፈተና ውስጥ የምትገባባቸው፣ ቅርቡን ነገ ሩቅ የሚያደርጉ፣ የሚያልፉ የማይመስሉ አጋጣሚዎችም ብዙ ናቸው።

ይህ የትዕግሥት አሰፋ በፈተና ያልተገታ የጽናት መንገድ ነው። ትዕግሥት አሰፋ በቅርብ ዓመታት በዓለም አትሌቲክስ እየተደጋገመ የቀጠለ የአንዲት ስኬታማ ኢትዮጵያዊት አትሌት መጠሪያ ነው።

አትሌቷ ከዓመታት በፊት በጎዳና ውድድሮች በተለይም አሁን በምትወዳደርበት ማራቶን የምትታወቅ አልነበረችም። በትራክ የረጅም ርቀት ውድድሮችም የእርሷ ዘርፍ አልነበሩም።

እ.አ.አ. በ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ ከመካከለኛ ርቀት ውድድሮች አንዱ በሆነው 800 ሜትር ኢትዮጵያን እስከመወከል የደረሰችው አትሌት የኋላ ኋላ በጉዳት ተፈተነች። በቅርብ ዓመታት በርካታ ስፖርተኞችን እየፈተነ ያለው የቋንጃ ጅማት ጉዳት (Achilles tendon rupture) የቀድሞዋን የመካከለኛ ርቀት አትሌትም ጎበኛት።

እ.አ.አ እስከ 2019 በጉዳቱ እየተፈተነች በተለያዩ ውድድሮች መሳተፏን ባታቋርጥም፣ ከ2019 በኋላ ግን ነገሮች ይበልጥ ተባባሱ። ሁኔታዋን የተከታተሉት በአውሮፓ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ጉዳቱ አስከፊ መሆኑን በመግለጽ ከዚህ በኋላ በስፖርት የመሳተፍ ዕድሏ ጠባብ መሆኑን፣ ለማብቃትም መቃረቡን አረዷት።

ያኔ የትዕግሥት ጽናት ተፈተነ፤ አትሌቷ ከስፖርት ሙሉ በሙሉ ርቃ በምታገግምባቸው ዓመታት የሁለት ሰዎች ሚና ጉልህ ነበር። የሕይወት አጋሯ ኢዮብ ኤሊያስ እና ስመጥሩ የአትሌቲክስ አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ።

የጉዳቱ ክብደት፣ የጊዜው ርዝመትም ሆነ የወደፊት የስፖርት ሕይወቷን ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ቃላት ከተለመችው ብሩህ ነገ አላስቀሯትም፤ እናም ተመለሰች።

ሁለት ዓመታት ከስፖርት ካስቀራት ጉዳት ስትመለስ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2022 በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ በመሮጥ 7ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች። ከዚያም እ.አ.አ በ2022 የበርሊን ማራቶን 2ኛ ተሳትፎዋን አደረገች።

በርካታ የዓለም ክብረ ወሰኖች የተመዘገቡባት በርሊንም ለማራቶን እንግዳ ሆና በርቀቱ 2ኛ ተሳትፎዋን የምታደርገውን አትሌት እጇን ዘርግታ ነው የተቀበለቻት። 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ በመግባት የመጀመሪያ ድሏን አሳካች።

በዓመቱም ተመልሳ 2023 ላይ ከነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ጌጤ ዋሚ ከዘመናት የድል መቼቶች አንዷ በሆነችው ምድር በርሊን በድጋሚ ባለድል ሆነች። በ2023ቱ ውድድር 2፡11፡53 በመግባት አሸናፊ ስትሆን፣ በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌይ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን ከ2 ደቂቃ በላይ በማሻሻል ጭምር ነው። በሴቶች የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰንን በማሻሻልም የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሆነች።

በበርሊን ማራቶን ለ2ኛ ተከታታይ ጊዜ ባለድል ሆና፣ በ2024 የለንደን ማራቶን የመጀመሪያ ተሳትፎዋ 2ኛ ደረጃን ካገኘች በኋላ፣ በ2025 እና 2026 ለንደን ላይ ደጋግማ ነገሠች። የሁለቱም ዓመታት የለንደን ውድድሮች ያለ አሯሯጭ ሴቶች ብቻ በሚወዳደሩበት ዘርፍ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ያስመዘገበችባቸው መሆኑም የተለየ ያደርጋቸዋል።

የ2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ እና የ2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትዕግሥት ኢትዮጵያን ወክላ የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበችባቸው ውድድሮች ናቸው።

ዛሬም ትዕግሥት በ52ኛው የበርሊን ማራቶን በሦስተኛ ተሳትፎዋ በሩት ቼፐንጌቲች የተነጠቀችውን የዓለም ክብረ ወሰን ዳግም በእጇ ታስገባለች ተብሎ ቢጠበቅም፣ በመጨረሻዎቹ ኪሎ ሜትሮች ባጋጠማት ጉዳት ምክንያት ይህን ሳታሳካ ቀርታለች። ሆኖም 2፡11፡04 በሆነ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።

በየትኛውም የሕይወት መስክ ፈተና ሲገጥም እጅ አለመስጠትን፣ ከመንገድ አለመቅረትን ብሎም ወደ ኋላ አለማለትን በቅርቦቹ ዓመታት ትዕግሥት አሰፋ በተጓዘችበት መንገድ የሚቀሰሙ ትምህርቶች ናቸው። ከዓመታት በፊት “መንገድሽ አብቅቷል” ስትባል ቀርታ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ውብ የድል ቀናት አይመጡም ነበር።

የሰው ልጅ አካሉ ቢሰበርም ልቡ ካልተሰበረ፣ አንገት ካላቀረቀረ፤ ከድሉ ደጃፍ ከውጥኑ ጫፍ መድረሱ የሚቀር አይደለም። የነዚህ ሁሉ የወድቆ መነሳት እና የጽናት ትዕምርቶች ባለቤት፣ የ2023 የዓለም ኮከብ አትሌት፣ የማራቶን ውድድሮች ንግሥት፣ የ2026 በርሊን ማራቶን አሸናፊ ትዕግሥት አሰፋ ተሰማ!

በእድሪስ አሕመድ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: