Search

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ፡ ከብሪክስ ስኬት እስከ ቀይ ባሕር ስትራቴጂያዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት

እሑድ መስከረም 17, 2019 92

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የምትከተለው ገለልተኛ እና ብዝሃ-ወገንን መሠረት ያደረገ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አዲስ የዲፕሎማሲ ስኬት ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ አቋም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በደቡብ-ደቡብ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ የአፍሪካን ድምፅ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መድረኮች በጉልህ ለማስደመጥ አስችሏል።

የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በዚህ የተሳካ ስትራቴጂ የዓለምን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚዛን የጠበቀ እና ብሔራዊ ጥቅሟን ያስቀደመ አቋም በመያዝ ወደፊት እየተራመደች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ጥቅሟን ማዕከል አድርጋ ባካሄደችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የብሪክስ አባልነቷን ከማረጋገጧም በላይ በስብስቡ ውስጥ ተደማጭ ሆናለች።

በቅርቡ በኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ ያደረገችው ንቁ ተሳትፎም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነቷን ወደ ላቀ ስልታዊ ተፅዕኖ ደረጃ አሸጋግሮታል።

በኒው ዴልሂ ጉባኤ የማጠቃለያ መግለጫ መሠረት፥ ኢትዮጵያ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ስታካሂደው የቆየችው እና በሚያዝያ 2018 ዓ.ም 7ኛ የሥራ ቡድን ስብሰባውን ያጠናቀቀችው የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር፣ የብሪክስ አባል ሀገራትን ሙሉ ድጋፍ አግኝቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ተጨማሪ ወንበር ለማግኘት የአፍሪካ ኅብረት እና የብሪክስ አባል ሀገራት የሰጡት ሙሉ ድጋፍ፣ እንዲሁም የ2027ቱን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በዋና አስተናጋጅነት እና በሊቀመንበርነት እንድትመራ መወሰኑ ዲፕሎማሲያዊ አቅሟን በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው።

በፋይናንስ ዘርፉም በአዲሱ የልማት ባንክ (NDB) አባልነቷን በማጠናቀቅ ላይ መሆኗ ለታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ እንድታገኝ በር የከፈተ ሆኗል።

ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በሀገር ውስጥ ገንዘቦች የንግድ ልውውጥ ለማድረግ የተጀመረው ውይይትም የውጭ ምንዛሬ ጫናን በመቀነስ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ነው።

ኢትዮጵያ ከእነዚህ ታላላቅ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ባሻገር የዓለምን ትኩረት በሳበው የቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካ ላይ ያሳረፈችው ተፅዕኖ እጅግ የጎላ ነው።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና የቀጣናው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ ታሪካዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ አጣዳፊ ኢኮኖሚያዊ እና ልማታዊ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ሀገራችን በዓለም አቀፍ መድረኮች አብራርታለች፤ ተደማጭነትም አግኝታለች።

በ1985 ዓ.ም ኤርትራ መገንጠሏን ተከትሎ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የባሕር በር ያጣች ቢሆንም፣ ለዚህ ወሳኝ ፍትሐዊ ጥያቄ የጋራ ልማትን መሠረት ባደረገ መልኩ በሰላማዊ ድርድር እልባት ለመስጠት የያዘችው ጽኑ አቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል።

በተለይም በቀይ ባሕር ደኅንነት እና አስተዳደር ላይ ኢትዮጵያን ለማግለል የሚደረጉ ጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በብልሃት ለመመከት የተወሰዱት እርምጃዎች እጅግ የተሳኩ ናቸው።

በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ "Will for Peace 2018" የባሕር ኃይል ልምምድ ላይ ያደረገችው ንቁ ተሳትፎም፣ የቀጣናው ሰላም እና ንግድ ያለ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ሊሳለጥ እንደማይችል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አመላክቷል።

እነዚህ ስኬታማ ክንውኖች በቀይ ባሕር፣ በኤደን ባሕረ-ሰላጤ እና በሕንድ ውቅያኖስ የንግድ መስመሮች ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ስትራቴጂያዊ ጥቅሞች በዘላቂነት እንድታስከብር የሚያስችሏት ጠንካራ መሠረቶች ናቸው።

ገለልተኛ እና ሁሉንም አሳታፊ ያደረገው ስትራቴጂያዊ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋም ኢትዮጵያን ከቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምጿ የሚሰማ፣ መብት እና ጥቅሟን በሰላማዊ መንገድ የምታስከብር እና የአፍሪካ ወኪልነቷ በብቃት የምትወጣ የዲፕሎማሲ ምሰሶ አድርጓታል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: