ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባህል ማዕከል ሆና የኖረች ገናና ሀገር ናት።
በጥንት ዘመን የነበራት የባሕር ይዞታና የባሕር ኃይል የበላይነት ለዘመናት የውጭ ወረራዎችን እንድትመክትና ብሔራዊ ጥቅሟን በጽኑ እንድታስከብር አስችሏት ነበር።
ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲቃኝ፣ በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያውያን በቀይ ባሕር ሁለቱንም ዳርቻዎች በመቆጣጠር እስከ የመን ድረስ የሚያስተዳድሩበትና የጦር መርከቦቻቸውን በኩራት የሚያሰማሩበት አቅም እንደነበራቸው ይነግረናል።
ይህ ታላቅ ገድል በዘመናዊው ታሪካችንም ተደግሞ፣ በ1947 ዓ.ም "የኢትዮጵያ ሮያል የባሕር ኃይል" በሚል ስያሜ ተቋቁሞ በምፅዋ ወደብ ላይ መኖሪያውን በማድረግ ጠንካራ ሥራ ጀምሮ ነበር።
በደርግ ዘመነ መንግሥትም በዘመናዊ ሚሳይል አጥቂ መርከቦች፣ የቶርፒዶ ጀልባዎችና ምድረ-ነክ መርከቦች በመደራጀት በአፍሪካ ስመ-ጥር ከሚባሉ የባሕር ኃይሎች አንዱ ለመሆን በቅቶ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ሆኖም በታሪክ አጋጣሚዎችና በተፈጸሙ የፖለቲካ ስህተቶች ምክንያት ሀገራችን ይህንን የባሕር በር አጣች። በተለይም በ1983 ዓ.ም የተከሰተው የመንግሥት መውደቅ በኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ታሪክ ላይ ትልቅ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ውሳኔ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል እንዲፈርስ፣ ውድ ሀብቱ እንዲዘረፍና በከፍተኛ ወጪ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲበታተኑ ተደረገ።
ኤርትራ ስትገነጠልም ምንም አይነት የህግና የዲፕሎማሲ ድርድር ሳይደረግ አሰብን ጨምራ ይዛ እንድትሄድ በመደረጉ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወደብ አልባ እንድትሆን ተፈረደባት።
ይህ ታሪካዊ ክስተት ያሳደረው ጫና ዛሬም ድረስ ቀላል አይደለም። በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ከሚከናወነው ጠቅላላ የንግድ ልውውጥ ውስጥ ወደ 10 በመቶ የሚሆነው በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ መስመር ይተላለፋል።
የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ ከ90 በመቶ በላይ የሚንቀሳቀሰውም በዚህ ስልታዊ የውሃ አካል በኩል ነው። በቀይ ባሕር አካባቢ የሚታየው የባሕር ላይ ወንብድና፣ ሽብርተኝነትና የውጭ ሀገራት ወታደራዊ ስፋት የሀገራችንን የንግድ መርከቦችና የኢኮኖሚ ደህንነት በእጅጉ ስጋት ላይ ጥሎት ቆይቷል።
ስለዚህ የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና፣ የኢኮኖሚና የደህንነት ጉዳይ እንጂ የቁጭት ታሪክ ብቻ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም።
ይህን ስልታዊ ክፍተት ለመሙላትና ብሔራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ በ2011 ዓ.ም በተደነገገው አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እንደገና እንዲቋቋም ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት በምክትል አድሚራል ክንዱ ገዙ ዕዝ እና አመራር ስር የባሕር ኃይሉ በሰው ኃይል ልማት፣ በናቪጌሽንና በኢንጂነሪንግ ሙያዎች አባላቱን በከፍተኛ ጥራት እያሰለጠነ ይገኛል።
በተጨማሪም በፍጣን ጀልባዎች የሚንቀሳቀሱ የማሪን ኮማንዶዎችን፣ ከውሃ በታች ግዳጅ የሚወጡ ዳይቨሮችን፣ እና በባሕር ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን የመመከት የቴክኒክ አቅሙን በሚገባ ገንብቷል።
ይህ አዲስ የባሕር ኃይል በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ አባል ሀገራት የባሕር ላይ ወታደራዊ ልምምድ ላይ በመሳተፍም ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱንና ዝግጁነቱን በኩራት አሳይቷል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባሕር ኃይልን መልሶ ማደራጀትና ማዘመን የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን፣ የ130 ሚሊዮን ህዝብን ኢኮኖሚያዊ ደህንነት የመጠበቅና ታሪካዊ ጥቅሟን የማስከበር ከባድ አደራ ነው።
ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ከትናንት እዳነት ተላቆ ወደ መጪው ዘመን ሀብትነትና የጋራ ልማት መሸጋገር ያለበት ወሳኝ ስልታዊ ቀጣና ነው።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: