"ባንዳ ለሆዱ ሲሞት፣ እኛ ግን ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለህዝቦች ክብርና አንድነት እንሞታለን" በማለት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ልጆች ፅኑ አቋም አረጋግጠዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንን የገለፁት በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ስለወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ለሠራዊቱ አመራሮች የሥራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ሻዕቢያ ከጅምሩ ኢትዮጵያን ከባሕር በር ለማራቅ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ደባ ሲሰራ የኖረ ኃይል መሆኑን ያነሱት ፊልድ ማርሻሉ፣ ህወሓትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በመሸጥ እና ለ27 ዓመታት ስልጣን ይዞ ሀገራችንን የባሕር በር አልባ በማድረግ የገዛ ሀገሩን ሠራዊት እስከማጥቃት የደረሰ የክህደት ኃይል መሆኑን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በህወሓት ክህደት ብትፈተንም፣ የልዩ ዘመቻ ሠራዊትን መሰል ጠንካራ የሀገር አርበኛ ልጆች ያሏት በመሆኗ ፈተናዎችን በድል ተሻግራ ጉዞዋን ቀጥላለች።
ፅንፈኞቹን ፋኖንና ኦነግ ሸኔን ጨምሮ አራቱም የጥፋት ኃይሎች በባዕዳን ስትራቴጂ ሥር ተሰልፈው ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ ጥምረት ቢፈጥሩም፣ ደካማ ኢትዮጵያን የማየት የከንቱ ምኞት ህልማቸው መቼም እንደማይሳካ በተግባር ታይቷል።
ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በመከፋፈል እና የትግራይን ህዝብ ከወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ ሲሰራ የኖረ እኩይ የፖለቲካ አራማጅ ነው።
ዛሬ ላይ ያ ሁሉ ሴራው ከሽፎ፣ የትግራይን ህዝብ ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን ቡድን መሰሪነት በመረዳቱ፣ ከህዝብ ተነጥሎ የቀድሞ ጠላቶቹን ሸኔንና ፅንፈኛ ፋኖን አቅፎ እንዲሁም ሻዕቢያን አዝሎ የትላንት ክህደቱን በአደባባይ እየደገመ ይገኛል።
በዚህም የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አባላት እነዚህ የጥፋት መልዕክተኞች በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የደቀኑትን ጥፋት በማምከን፣ እብሪታቸውን ማስተንፈስና የጥፋት እግራቸውን መስበር እንዳለባቸው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አሳስበዋል።
በተለይም የህወሓትን፣ የፋኖንና የሸኔን የተላላኪነት ሚና መሰባበር የሻዕቢያንና የግብረ አበሮቹን ተስፋ ማጨለም እንደሆነ በማስረዳት፣ ሠራዊቱ ከአያቶቹ የቀዳውን አርበኝነት በተግባር እንዲያሳይ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት በትጥቅም ሆነ በሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፣ ለሰፈር ባንዳዎች ብቻ ሳይሆን፣ በየትኛውም አቅጣጫ በሀገር ላይ ለሚቃጣ ማናቸውም ጥቃት ፈጣንና አስተማማኝ ምላሽ ለመስጠት ሙሉ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ደጀንነት የጀመረችውን የእድገትና የብልፅግና ጉዞ ወደፊት ትቀጥላለች፤ የታሪካዊ ጠላቶቿ ህልምም መቼም አይሳካም ሲሉ መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: