Search

ከዳሞታ ጫፍ እስከ ኦሞ ሸለቆ የብዝሃነትና የተፈጥሮ ፀጋዎች መዲና የሆነችውን ደቡብ ኢትዮጵያን በምናብ እንቃኝ

ቅዳሜ ነሐሴ 09, 2018 46

በተፈጥሮ መስህቦቿ፣ በጥንታዊ ታሪኮቿ እና በ32 ነባር ብሔረሰቦች ውብ ባህላዊ ዕሴቶች አጊጣ የምትገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማትና ነባር ቅርሶቿን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስመዝገብ ዋነኛ የቱሪዝም ማዕከል እየሆነች ትገኛለች።

ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴሬሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ የተመሠረተው ይህ ክልል፣ በ12 የዞን መዋቅሮች እና በ6 የክልል ማዕከላት ለዘመናት በአብሮነትና በህብረት የኖሩ ህዝቦችን አቅፎ የብዝሃነት ውበትን በተግባር እያሳየ ይገኛል።

ክልሉ የበርካታ ህዝቦች የጋራ መኖሪያ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ብሔረሰብ ባለው ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርስ ለአካባቢው ብሎም ለሀገራችን አዲስ የባህልና የታሪክ ቀለም በመስጠት ላይ ይገኛል።

ወደዚህ አስደናቂ ምድር ስንጓዝ የተፈጥሮና የባህል ውህደት ዓይኖቻችንን ይማርካሉ። ጉዟችንን በወላይታ ህዝቦች ግርማ ሞገስ በሆነው የዳሞታ ተራራ እና በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የጊፋታ በዓል ስንጀምር፣ ቀጥሎ የጋሞ ህዝቦችን በአባያና ጫሞ ሀይቆች ዳርቻ፣ በሰላም አባቶቻቸው እና በደማቁ የዮ ማስቃላ በዓል እናገኛቸዋለን።

ለዓለም በምሳሌነት በተመዘገበው የጥምር ግብርና ሥርዓት፣ በይርጋጨፌ ቡና እና በዳራሮ በዓል የጌዴኦ ህዝቦችን ስናደንቅ፣ በግብርና ምርቶቻቸው እና በጋዜ ማስቃላ ደግሞ የጎፉ ህዝቦችን ማንነት እንማረካለን።

ጉዟችን ወደ ኦሞ ወንዝ ሲያቀና የደቡብ ኦሞ ህዝቦችን የብዝሃ ባህልና ቋንቋ ቀለማት እናያለን፤ ከዚያም አልፎ ዓለምን ባስደመመው ድንቅ የእርከን ሥራቸው የኮንሶ ህዝቦችን፣ በባህላዊ እሴቶቻቸው የቡርጂ ህዝቦችን፣ በጋዮ ፏፏቴ የኤሌ ህዝቦችን እንዲሁም እህልን ለዓመታት በጥራት በማቆየት የጎተራ ጥበብና በ"ፊላ" ሙዚቃቸው የዴራሼ ህዝቦችን እናስሳለን።

ልዩ በሆነው የአለባበስ እና የባህል ስርዓታቸው ደግሞ የባስኬቶ ህዝቦች የዚህን ክልል ህብረ-ቀለም ይበልጥ ያደምቁታል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለጎብኝዎች ድንቅ አግራሞትን የሚጭሩ ሌሎች በርካታ የመስህብ ስፍራዎችንም አቅፏል። የጉጌ ተራሮች እና የ360 ዲግሪ ተሽከርካሪ ጉጌ ሬስቶራንት፣ ዲሽታ ጊና፣ የቦቼና ቦራጎ እንዲሁም የጎሌ ዋሻዎች፣ የትክል ድንጋዮች፣ ማራኪው መልክዓምድር፣ እና እንደ ነጭ ሣርና ማዜ ያሉት ብሔራዊ ፓርኮች የተፈጥሮን ድንቅ ስጦታዎች ያሳያሉ።

በዶርዜ መንደር በዝሆን ራስ ቅርጽ የተገነቡት የቀርከሃ ቤቶች፣ "የእግዜር ድልድይ" ተብሎ የሚጠራው የተፈጥሮ መሻገሪያ፣ ማራኪ የሽመና ጥበባት፣ የዘመን መለወጫ በዓላት እና የዕርቅ ስርዓቶች ጎብኚዎችን ወደ ሌላ ዓለም የሚወስዱ የክልሉ ውድ ሀብቶች ናቸው።

ክልሉ ከተመሠረተበት ማግስት ጀምሮ ነባር እሴቶቹን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ስኬት አስመዝግቧል። የጌዴኦ ባህላዊ የመሬት አጠቃቀም ጥምር ግብርና እና የወላይታ ጊፋታ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ከማድረጉም ባለፈ፣ ቀድመው የተመዘገቡትን የኮንሶ የእርከን ስራ እና የታችኛውን የኦሞ ሸለቆ ቅርሶች ጠብቆ በማቆየት የቱሪዝም አድማሱን እያሰፋ ይገኛል።

ብዝሃነትን አንፀባርቀው በልዩነቶቻቸው ደምቀው የሚኖሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቦች፣ በመመካከርና ልዩነትን ለአንድነት አቅም በማድረግ አብሮ የመኖር ትልቅ ማሳያ ናቸው።

በመሆኑም ሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ያላችሁ የቱሪዝም አፍቃሪያን፣ ይህንን ድንቅ የባህል፣ የተፈጥሮ እና የታሪክ ባለቤት የሆነውን ማራኪ ክልል በመጎብኘት የማይረሳ የህይወት ትዝታን እንድትሰንቁ ተጋብዛችኋል።

በትዕግስቱ ቡቼ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: