Search

በጠረጴዛ ዙሪያ የሚፃፍ አዲስ ታሪክ፡- ለዘላቂ ብልፅግና እና ለጋራ ኅልውና የተጣለ ወሳኝ መሰረት

ቅዳሜ ነሐሴ 09, 2018 47

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ካስተናገደቻቸው ልዩ የመግባቢያ እና የጋራ ሀገራዊ ራዕይ የመቅረጫ ምዕራፎች መካከል አንዱ በመሆን ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተወጣጡ 4 ሺህ ተመካካሪዎችን ሰብስቦ በስኬት እየተካሄደ ይገኛል።

ይህ ታሪካዊ መድረክ በስምንት ወሳኝ ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ ሕዝብ በወኪሎቹ አማካይነት በግልፅ የሚወያይበት፣ በምክንያት የሚሞግትበት እና ሀገራዊ የጋራ መግባባት ላይ የሚደርስበት ታላቅ ሀገራዊ አጋጣሚ ነው።

በአሁኑ ወቅት የምክክር ሂደቱ ተመካካሪዎች በጥልቀት የሚመክሩበት እና የልዩነት ማዕዘኖችን አጣጥመው የጋራ መግባቢያ ሐሳቦችን ለመለየት ውይይት የሚያደርጉበት ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛሉ። ይህ ታሪካዊ ሂደት ከአሃዞች በላይ ከጀርባው የበርካታ ሰዎችን ትዕግስት፣ የመደማመጥ ባህል፣ የጋራ ፅናት እና ሀገር የመገንባት ራዕይን የያዘ ታላቅ ምዕራፍ ነው።

በምክክሩ የሚሳተፍ እያንዳንዱ ተመካካሪ የራሱ የሆነ ታሪክ እይታ እና የህይወት ተሞክሮ ያለው ቢሆንም፣ "የሀገሬን ኅልውና በዘላቂ መሰረት ላይ ማፅናት አለብኝ" በሚል የላቀ መርህ ሐሳብን በሐሳብ በመርታት እውነተኛ ባለሀገርነቱን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ የፈተና እና የድል ምዕራፎችን አሳልፋ ዛሬ ላይ ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞዋን እያፋጠነች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ሁሉም ዜጎች ለጥያቄያቸው ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት በመመካከርና በመወያየት እንጂ በጠብመንጃ እንዳልሆነና "አሸናፊው እከሌ ተሸናፊው እከሌ" የሚባልን ታሪክ ለመቋጨት የፅኑ አቋም መግለጫ ሆኗል።

ተመካካሪዎቹ በጠረጴዛ ዙሪያ ከሚደረጉ ውይይቶች ባሻገር ከውስን ሐሳቦች ወጥተው የሁሉንም ወገን ኅልውና እና ደኅንነት ቀዳሚ በማድረግ ልዩነቶችን እንደ ፀጋ በመቁጠር እና ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት በመመራት ሀገራዊ አንድነትን በተግባር እየተረጎሙት ይገኛሉ።

ይህ የቁርጠኝነትና የሀገር ፍቅር መንፈስ የሰዎችን የግል አመለካከት ከፍ ወዳለ ሀገራዊ ራዕይ በማሸጋገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን የሚያስፍን እንዲሁም የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጥ ቁልፍ ምዕራፍ ከፍቷል።

በመሆኑም እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የዛሬን ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት ብቻ ሳይወሰን የጋራ ግንዛቤን በማሳደግ በሰላም፣ በፍትህ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የሚያስችል ታሪካዊ መሰረት እየጣለ ይገኛል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: