Search

ከምናብ ወደ ተጨባጭ ግዝፈት የመደመር ፍልስፍና በኢትዮጵያ ቱሪዝም የፈጠረው አዲስ አድማስ

ቅዳሜ ነሐሴ 09, 2018 56

ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶችና ለውጦች ሁልጊዜም የሚጀምሩት ከትንሽ ሀሳብ እና ከምናብ ነው። "መደመር" ከምናብ የሚጀምር፣ አሻግሮ ተመልክቶ ተስፋን የሚዘራ፣ ዛሬን ከትንሹ የሚጀምር፣ ዘላቂና የማይነጥፍ አድርጎ የሚሠራ ፍልስፍና መሆኑ ከታየባቸው ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ኢንደስትሪ ዋነኛው ነው።

ይህ እሳቤ አንድን ትንሽ ዘር መሬት ላይ በመዝራት፣ ያቺ ዘር አድጋ እንዴት የዋርካ ያህል ግዙፍ አካል ይዛ ለብዙዎች መጠለያ፣ ማረፊያና መደገፊያ እንደምትሆን በተግባር አሳይቶናል።

የሀገራችን አዲሱ የቱሪዝም እና የፓርክ ግንባታ ጉዞ የዚህ የተግባር ፍልስፍና ህያው ማሳያ ነው። ጥቂት ጊዜና አነስተኛ ሀብት በመጠቀም ከቤተ መንግሥት ግቢን ከማስዋብ የጀመረው የፓርክ ሥራ፣ ዛሬ አድማሱን አስፍቶ በእያንዳንዱ ክልል ተዳርሷል።

በወቅቱ እንደ አንድ ቀላል የማስዋብ ተግባር ተደርጎ የተጀመረው ይህ ጥረት፣ አሁን ላይ ሀገራችንን የሰፉና እጅግ አስደማሚ ፓርኮች ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል።

ዛሬ ላይ በሀገራችን እየተገነቡና እየተመረቁ ያሉ ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻዎች የዜጎችን የመዝናናት መብት ከማረጋገጥ ባሻገር፣ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ሞተር እየሆኑ ይገኛሉ።

እነዚህ ዘመናዊ የቱሪዝም መስህቦች የኢትዮጵያን ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋዎች ከዘመናዊነት ጋር በማዋሃድ የሀገሪቱን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየሩት ነው።

ፕሮጀክቶቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠር፣ መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት እና የስነ-ምህዳር ጥበቃን ከማረጋገጥ አኳያ ያላቸው ሚና እጅግ የጎላ ነው።

ከዚህም በላይ፣ አዲሱ ትውልድ በሀገሩ ተፈጥሮና ውበት እንዲኮራ፣ እንዲሁም የተሻለች ኢትዮጵያን አሻግሮ እንዲመለከት ትልቅ የስነ-ልቦና መነቃቃትን ፈጥረዋል።

ከትንሽ ጅምር ተነስተን በትልቅ ራዕይ ከተጓዝን የማይደረስበት ከፍታ እንደሌለ የቱሪዝም ዘርፉ አስደናቂ ስኬት ቋሚ ምስክር ነው።

ይህ ከቤተ መንግሥት የተጠነሰሰ የልማት ብርሃን፣ ዛሬ መላ ኢትዮጵያን እያዳረሰ የሁለንተናዊ ብልጽግናችን ጠንካራ መሰረት ሆኗል።

በቀጣይም ይህ አዲስ ሀገራዊ የቱሪዝም ባህል ይበልጥ ጎልብቶ፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ እና የዓለም ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚያደርጋት አያጠራጥርም።

በጌቱ ላቀው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: