ወጣት ጋሻው ኤዶም ይባላል። የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ነው። በመካኒካል ምህንድስና ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የመንግሥት ስራን ከመፈለግ ይልቅ በሀዋሳ ከተማ በማህበር በመደራጀት ወደ ማሽን ማምረት ስራ ገባ።

ማህበሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አርሶአደሮችን ህይወት በቀላል ማሽነሪዎች ማዘመን እና ትርፋማ ማድረግ ይቻላል የሚል አቋም በመያዝ የተለያዩ የግብርና መሳሪያዎችን እያመረተ ነው።
ጋሻው እና ጓደኞቹ የሰሩት የእርሻ ትራክተር የትኛውም አርሶአደር በራሱ ሊያንቀሳቅሰው የሚችል ሲሆን በቀን እስከ አራት ሄክታር ማሳ ማረስ ያስችላል።

ወጣት ጋሻው ማህበራዊ ሚዲያው የፈጠረውን ዕድል እንደ ገበያ በመጠቀም፤ ማህበሩ አዳዲስ ፈጠራዎችን ይማራል፤ ምርቱን ያስተዋውቃል፤ ትዕዛዝ ተቀብሎ ይሰራል ሲል ገልጿል።
ሌሎች ወጣቶችም ወቅቱ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም እና ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ባለመሸነፍ ትልቅ ሀብት መፍጠር እንደሚችሉም ወጣት ጋሻው ምክሩን ለግሷል።
በአስረሳው ወገሼ