Search

አፍርሶ ከመጀመር ወደ መደመር፦ የጸና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሀገራዊ ጥረት

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 98

ኢትዮጵያ ሺህ ዘመናትን ያስቆጠረ የሀገረ መንግሥት ታሪክ ቢኖራትም ከተቋማት ይልቅ ግለሰቦች እና ፓርቲዎች በሚገዝፉበት የፖለቲካ ባህል ምክንያት ጠንካራ እና የጸና ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ስትፈተን ኖራለች።

መንግሥታት ሥልጣን ሲይዙ የነበረውን አፍርሰው ከዜሮ መጀመርን በመምረጣቸው ሀገራችን ያልተቋረጠ የመንግሥት ሥርዓት ቢኖራትም ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት እውን ማድረግ ሌላኛው ፈተና ነበር።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህንን "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" የሚል አፍራሽ የፖለቲካ ባህል በመቀየር፣ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ደግሞ ከነገ በሚያስተሳስር ዕሳቤ ቀጣይነት ያለው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጓል።

ይህ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን የፖለቲካ ሥርዓቶች ሲቀየሩ የማይፈርሱ ነጻ እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እንዲሁም ሕዝቦችን የሚያስተሳስር ገዥ ትርክት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል።

በታሪካችን በደርግ ዘመንም ሆነ በኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን የሀገራችን ቁልፍ ተቋማት የየሥርዓቱ ርዕዮተ ዓለም አስፈጻሚዎች ነበሩ።

መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት እና ሌሎችም የዴሞክራሲ ተቋማት ኢትዮጵያን ከመምሰል ይልቅ ገዢ ፓርቲዎችን እንዲመስሉ ተደርገው ነበር።

አሁን ግን ይህንን ስብራት ለመጠገን የመደመር ዕሳቤ አፍርሶ የመጀመርን ልማድ በማስቆም ጠንካራ ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት ላይ ይገኛል።

በዚህ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ሲገልጹ "መደመር አፍርሶ የመጀመር የፖለቲካ ባህል ለኢትዮጵያ አይጠቅምም፤ መቆም አለበት ብሎ ያምናል" ብለዋል።

ለምሳሌ የመከላከያ ሠራዊቱ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ተላቅቆ፣ የሀገርን እና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ወደሚያስጠብቅ ኢትዮጵያን ወደሚመስል ነጻ ተቋምነት እየተቀየረ ነው።

ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ሊገነባ የሚችለው እንዲህ ዓይነት ብቃት ያላቸው፣ ገለልተኛ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩ ጽኑ ተቋማት ሲኖሩ ብቻ መሆኑን የአሁኑ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ያሳያል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ማንነቶች፣ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች መኖሪያ እንደመሆኗ ይህንን ብዝኃነት ለልዩነት ማራገቢያነት ከመጠቀም ይልቅ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማጽኛነት መጠቀም የግድ ይላል።

በመሆኑም ከተቋማት ጥንካሬ ጎን ለጎን የጸና ሀገረ መንግሥት መሠረቱ አስተሳሳሪ ገዥ ትርክት ላይ ትኩረት ማድረግም ያስፈልጋል።

ይህ ገዥ ትርክት አንዱን አግልሎ ሌላውን የሚያነግሥ ስላልሆነ የጋራ ታሪክን፣ ሥነ ልቦናዊ ትሥሥርን እና የጋራ ዕጣ ፈንታን የሚያጎላ ነው።

ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይም እኩል ባለቤትነት እንዲሰማቸው ማድረግ የሚቻለው ሁሉም ራሱን የሚያይበት ሀገራዊ ትርክት መፍጠር ሲቻል ብቻ መሆኑ እሙን ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጅምር ከግብ ሊደርስ የሚችለው ያለፉትን ስህተቶች በማረም፣ የተገኙ ድሎችን በማስፋት እና ለነገው ትውልድ የሚጠቅም ሐሳብን በማበርከት ነው።

ስለዚሁ ዕሳቤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አክለው ሲያስረዱ፣ "ለዛሬ እና መጪው ትውልድ ጥቅም እና ፍላጎት የሚሠራ ሐሳብ እና ተቋም፣ ማቆየት ያስፈልጋል" በማለት አስምረውበታል።

የሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ብዝኃነትን ያከበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስፈን የሕዝቦችን እኩልነት ያረጋግጣል።

የትናንቱን ጠባሳ ሽሮ፣ የዛሬውን አቅም አሟጥጦ በመጠቀም፣ ሀገራዊ መግባባትን እና ጠንካራ ተቋማዊ አሠራርን በማዋሐድ፣ የማይናወጥ እና በትውልድ ቅብብሎሽ የሚጸና ሀገረ መንግሥት መገንባት የዘመኑ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: