ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ መኖሪያና የጥንታዊ ነፃ ሀገረ መንግስታት መሰረት የሆነችው ኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ የህዝብ ብሶቶችን፣ የፖለቲካና የታሪክ ስብራቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ያለመ አዲስና ታሪካዊ የምክክር ምዕራፍ ውስጥ ትገኛለች።
በመንግስት፣ በፖለቲካ ተዋናዮች፣ በማህበረሰቦችና በዜጎች መካከል የቆዩ ቅራኔዎችን በውይይት ለመፍታት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚመራው ይህ አሳታፊና አካታች ሀገራዊ መድረክ ከግጭት አዙሪት በማውጣት ወደ ታላቅ የጋራ ብልፅግና የሚያሸጋግር ፍቱን መድሀኒት በመሆን በመተግበር ላይ ይገኛል።
ሀገር የምትገነባውና የምትመራው በሀይልና በጠመንጃ ሳይሆን በሰከነ ውይይትና በህግ ፅኑ መሰረት ላይ መሆኑን ያለፈው የታሪክ እልቂትና ውድመት ህያው ምስክር ሲሆን።
በዚህም መሰረት ሀገር በቀል እውቀቶችንና ሀገረሰባዊ እሴቶችን ማእከል በማድረግ እየተካሄደ ያለው ይህ ሀገራዊ ምክክር የአሸናፊና ተሸናፊ ትርክትን በማስቀረት የሁሉም ዜጎች ድምፅ እኩል የሚሰማበትንና ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ባህል እየገነባ ይገኛል።
የጀመርነውን የሰላም ጉዞ ለማስተጓጎልና ጥርጣሬን ለመዝራት ከእውነታ የራቁ አሉባልታዎችና አሉታዊ ሀሳቦች ከተለያዩ አካላት ቢሰነዘሩም፣ እነዚህ ከንቱ መፍጨርጨሮች የህዝቡን እውነተኛ ፍላጎት የማይወክሉና ሂደቱን ሊያስተጓጉሉት የማይችሉ ናቸው።
ይህ የምክክር ሂደት የአንድ ጊዜ ሁነት ሳይሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ሀይሎች በሂደት እያሳተፈ የሚቀጥል የረጅም ጊዜ ጉዞ ነው።
የትናንት ቅራኔዎችን ባሳተፈ መንገድ በመፍታት የሚገነባው ዘላቂ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት፣ የውስጥ ችግሮችን በውይይት የመፍታት አቅምን ለማሳደግና ወደፊት ለሚካሄዱ ምርጫዎችና የፖሊሲ ውይይቶች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በተጨማሪም የተረጋጋ ፖለቲካዊ ምህዳር መፈጠሩ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፎች ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ለጠንካራ ኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ይጥላል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን፣ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመረችው ይህ ጥረት አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው ለመፍታት ለሚያደርጉት ጥረት መልካም አርአያ ከመሆኑም በላይ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድን ለማረጋጋትና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ታሪካዊ ግብ ይመታ ዘንድ የመንግሥት፣ የፖለቲካ ሀይሎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ ሚዲያና የመላው ዜጎች ቅንጅታዊ አሰራርና ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ከግጭት ይልቅ ውይይትን፣ ከመለያየት ይልቅ መግባባትን በማስቀደም ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም ለዛሬ ሰላማችን ብቻ ሳይሆን ለነገዋ የበለፀገች ኢትዮጵያና ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መሰረት የመጣል ሀላፊነት የሁላችንም እንደሆነ ይታመናል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: