Search

የብርሃኑ ማበሰሪያ፣ የኢትዮጵያውያን የሃይማኖት፣ የባህል እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ድልድይ - ቡሄ

ረቡዕ ነሐሴ 13, 2018 84

በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የነሐሴ አጋማሽ ሲደርስ እና አዲሱ ዓመት ደጃችን ላይ ሲያንኳኳ ከየሰፈሩ እና ከየኮረብታው አናት የሚሰማው የጅራፍ ድምፅ የክረምቱ ጭጋግ ተገፎ የብርሃን ወጋገን የሚታይበት "ቡሄ" በዓል መቃረቡን ያበስራል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ የታየውን መለኮታዊ ብርሃን ለማሰብ "ደብረ ታቦር" ተብሎ የሚጠራው ይህ በዓል፣ በባህላዊ ትርክቱ ደግሞ "ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት" እንደሚባለው ሁሉ የዝናብ እና የጨለማው ወቅት ማለፉን፣ የልምላሜ እና የብርሃን ዘመን መምጣቱን የሚያበስር የተፈጥሮ ለውጥ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

ገና በሐምሌ ማጠናቀቂያ ላይ ሕፃናት ጅራፍ ገምደው ማጮህ የሚጀምሩ ሲሆን በሃይማኖታዊ ትርጓሜው መለኮታዊውን ድምፅ በባህላዊው ገጽታ ደግሞ የልጆችን ጥንካሬ የሚያንጸባርቀው በየሸለቆው የሚንጠሸጠሸው የጅራፍ ድምፅ የበዓሉን መቃረብ ያበስራል።

በበዓሉ ዋዜማ ወጣቶች እና ሕፃናት በየቡድናቸው ሆነው ከቤት ወደ ቤት እየዞሩ "ሆያ ሆዬ" እያሉ የሚያዜሙት ግጥም እና ዜማ በየቤቱ ደስታን የሚጭር እና የበዓሉን ድባብ የሚያደምቅ ሲሆን ይህም ሥነ ሥርዓት ለሕፃናት የመጋራት የእኩልነት እና የኅብረት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥበት ነው።

በተጨማሪም በኮባ ተጠቅልሎ የሚጋገረው እና ልዩ መዓዛ ያለው ሙልሙል ዳቦ የእናቶች የፍቅር ስጦታ ሆኖ በሕፃናት ዘንድ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቅ የበዓሉ ዋና አካል ነው።

ቡሄ የትውልድ ቅርስን ከወጣቶች ተሳትፎ፣ ከጉርብት እና እና ከማኅበራዊ ትሥሥር ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የአንድ አካባቢ ባህል ብቻ ሳይሆን በባህላዊ ልዩነቶች መካከል የጋራ ዕሴቶችን ለማጠናከር የሚያግዝ የባህል ሀብት ነው።

የመረዳዳት፣ የመጎብኘት፣ የመካፈል እና የጉርብትና መንፈስ በበዓሉ አከባበር ውስጥ በግልጽ የሚንጸባረቅ ሲሆን በዚህም መልኩ የትናንትን ባህል ለዛሬ ትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ የተለያዩ ባህሎች እና ማኅበረሰቦች በጋራ ሊያከብሯቸው የሚችሉ ዕሴቶችን ያሳያል።

ስለሆነም ቡሄ በዜማ፣ በጭፈራ እና በደስታ ብቻ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ ፍቅርን፣ የጎረቤት ትሥሥርን፣ የትውልድ ቅርስን እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የኢትዮጵያ ባህላዊ ሀብት ነው።

ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባህል እና በሃይማኖታዊ ትውፊቶች ያጌጡ ብዝኃ በዓላት ባለቤት እንደመሆኗ መጠን እነዚህ ክብረ በዓላት መንፈሳዊ ጥልቀታቸውን ጠብቀው ከማኅበራዊ ትሥሥር ማጠናከር ባለፈ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጎብኚዎች የማይረሳ ትዝታን የሚፈጥሩ፣ የቱሪዝም ኢኮኖሚን ከፍ የሚያደርጉ ድንቅ ጸጋዎች ናቸው።

እንኳን ለደብረታቦር (ቡሄ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በብሌን ደምበሎ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: