Search

ህወሓትን እንደ ጨው ቀምሰን አይተነዋል፤ ከግጭት ውጭ አንድም የሚጠቅም ሀሳብ የለውም - የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጁነዲን ሳዶ

ማክሰኞ ነሐሴ 12, 2018 148

ህወሓትን እንደ ጨው ቀምሰን አይተነዋል፤ ከግጭት ውጭ አንድም የሚጠቅም ሀሳብ የለውም ሲሉ የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጁነዲን ሳዶ ገለጹ።

አቶ ጁነዲን ሳዶ፥ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሀገር በሚያስተዳድርበት ዘመንም አንዱን ሕዝብ ከሌላው ጋር በማቃረን ለሕዝቦች መቃቃር ምክንያት ሲሆን መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይም በታሪካዊ ጠላቶች በመታዘል የትግራይ ሕዝብን ለከፋ ሰቆቃና መከራ ዳርጎታል ነው ያሉት።

ህወሓትን እንደ ጨው ቀምሰን አይተነዋል፤ አብረንም ሰርተናል፤ ከግጭትና ጥፋት ውጪ ለሀገር የሚጠቅም አንድም ሀሳብ የለውም ብለዋል።

ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በሀገራችን ለዘመናት የዘለቀውን የግጭት አዙሪት ከማስቀጠል ውጭ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አንድም አዎንታዊ ሀሳብ የሌለው እና ሀገርን ለማወክ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተሰለፈ አጥፊ ስብስብ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሕገ-ወጡ ቡድኑ "እኔ ካልገዛሁ" የሚለውን ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ተሸክሞ ታጣቂዎችን በማደራጀት ሀገር ለማመስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የትም የማያደርሰው ከንቱ ልፋት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በየትኛውም ሀገር አንድ ሕጋዊ ሠራዊት ብቻ የሚኖር መሆኑ እየታወቀ ቡድኑ እየተከተለው ያለው የትዕቢት እና የአጥፊነት መንገድ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚያጋጨው መሆኑንም ገልጸዋል።

ሕገ-ወጡ ቡድን ያለው አማራጭ ከጥፋት ጎዳናው ተመልሶ ወደ ሰላም መምጣት ብቻ መሆኑንም የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጁነዲን ሳዶ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: