የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከስምንቱ የምክክር ቡድኖች የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን ወደ አንድ ወጥ ሰነድ የማጠናቀር ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ እና ሂደቱም ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከስምንቱም ቡድኖች የተወጣጡ 120 አጠናቃሪ ተሳታፊዎች ያከናወኑት የአጀንዳ ማጠናቀር ሥራ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ የተወሰነ ጊዜ ፈጅቷል።
ይሁን እንጂ አጠናቃሪዎቹ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ ባደረጉት ርብርብ የስምንቱንም ቡድኖች ምክረ ሐሳብ ያካተተ አንድ ወጥ ሰነድ ማዘጋጀት ችለዋል።
በተዘጋጀው አንድ ወጥ ሰነድ ላይ ውይይት ለማድረግ በዛሬው ዕለት ለየቡድኖቹ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ ይህ አሠራር እያንዳንዱ ቡድን በሚቀርበው ሰነድ ላይ አስተያየቱን እና የመጨረሻ ግብዓቱን እንዲሰጥ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚሁ መሠረት ዛሬ ምሽት 120ዎቹ አጠናቃሪዎች ከስምንቱም ቡድኖች የሚሰጡትን የመጨረሻ ግብዓቶች በማካተት የሰነድ ዝግጅቱን ሙሉ በሙሉ ያጠናቅቃሉ።
በነገው ዕለትም ይህ የተጠናቀረው የመጨረሻ ሰነድ ለአራት ሺህ ተሳታፊዎች በይፋ እንደሚቀርብ እና ይህም በምክክር ሂደቱ አንድ ትልቅ ምዕራፍ ላይ መደረሱን የሚያሳይ መሆኑን ወይዘሮ ሒሩት አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተዛቡ መረጃዎችን በመስማት እንዳይወዛገብ እና ትክክለኛ የሆኑ ሚዲያዎችን እንዲሁም የኮሚሽኑን ይፋዊ መግለጫዎች ብቻ እንዲከታተል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: