ኢትዮጵያ ለሺሕ ዘመናት በባለቤትነት ይዛ የቆየችውን ቀይ ባሕር ያጣችበት አጋጣሚ ከውጭ ጠላት ጥቃት ይልቅ በውስጥ መዘናጋትና አንድነት መጥፋት የመጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህ የታሪክ እውነት የኢትዮጵያን ያለፈ ጉዞ ፍጹም በሆነ መነፅር የሚያሳይ እንዲሁም ለአሁኑ እና ለወደፊቱ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ሀገራዊ ማሳሰቢያ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ታላላቅ ሥልጣኔዎችን የገነባችው፣ ከእስያ እና ከአውሮፓ ጋር የንግድ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ያጠናከረችው በባሕር በሮቿ አማካኝነት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።
ነገር ግን ይሄን ታላቅ ጸጋ ያጣችው ከውጭ ኃይላት ጥንካሬ ይልቅ፣ በውስጥ ክፍተት፣ በፖለቲካዊ መበታተን እና በስትራቴጂካዊ መዘናጋት ምክንያት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ እንድትሆን ያደረጓት ክስተቶች የረጅም ጊዜ የውስጥ ድክመቶች ውጤት ናቸው። በልዩነቶች ላይ ያተኮረ የውስጥ ፖለቲካ ሀገራዊ ስትራቴጂን በመዘንጋቱ ለወደፊቱ ትውልድ የሚተርፍ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ አስከትሏል።
ይህም የባሕር በር የኅልውና፣ የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት መሆኑን ዘንግቶ ሀገራዊ ጥቅምን አሳልፎ መስጠት ሲሆን፣ ይህ የታሪክ ምጸት የሚያሳየን አንድ ነገር ቢኖር የውጭ ጠላቶች ሁልጊዜም የሚጠቀሙት የውስጥን ክፍተት ነው የሚለውን መርህ ነው።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ፣ የታሪክ ስህተትን ለማረም እና የሀገራችንን የወደፊት የኢኮኖሚ ኅልውና ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር የባሕር በር አልባ ሆና መቆየቷ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ቢሊዮን ዶላሮች ከመጨመሩም በላይ፣ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ያላትን ተወዳዳሪነት ገድቦታል።
በአሁኑ ወቅት ፍጹም በሆነ የሰላም፣ የትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት (Win-Win) መርህ ላይ በመመስረት የባሕር በርን ለመግኘት እየተሠራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ለራሷ ብቻ ሳይሆን፣ ለጎረቤት ሀገራትም የኢኮኖሚ ዕድገት እና የቀጣናው መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ፍትሐዊ የንግድ እና የባሕር በሮች አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻልም ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት የአደባባይ ሐቅ ነው።
በውስጥ መዘናጋት ያጣነውን የባሕር በር መልሰን ልናስከብረው የምንችለው ደግሞ በጠንካራ የውስጥ አንድነት፣ በተሰናሰለ ዲፕሎማሲ እና በጽኑ ሀገራዊ ራዕይ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የኅልውና እና የወደፊት ትውልድ ዕድልን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው። ታሪክ የሚያስተምረን ክፍተታችን ለኪሳራ እንደዳረገን ሁሉ፣ አሁናዊው አንድነታችን ደግሞ የታጣውን የታሪክ ባለቤትነት እንደሚያስመልስ ነው።
በመሆኑም አሁን እያካሄድን ባለው የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስኬታማ ለመሆን፣ ከምንም በላይ የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር፣ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እና ለጋራ ሀገራዊ ጥቅም በአንድነት መቆም ወሳኝ እና ፈጣን ተግባራችን ሊሆን ይገባል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: