የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ የተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ታላቅ ስኬት መሆኑን በመግለጽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ ልማት፣ የዜጎችን ደኅንነት እና ደስታ ለማረጋገጥ ሰላም፣ ፀጥታ እና መረጋጋት ማስፈን ወሳኝ ነው ብለዋል። "ሰላም እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ማንኛውንም ዋጋ ልንከፍልለት ይገባል" ያሉት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ ሀገራዊ ምክክሩም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፍ አራት ዓመታት መውሰዱ እና 4000 የሚጠጉ ሰዎች መሳተፋቸው የሒደቱን አሳታፊነት እና ትልቅነት እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
የምክክሩ መፍትሔ ሐሳቦች ብሔራዊ አንድነትን፣ ትሥሥርን እና ልማትን ለማሳካት በጥንቃቄ እና በቅንነት ሊተገበሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ኅብረት በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው ኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት በሙሉ ልብ ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ መሆኑን እና ዘወትር ከኢትዮጵያውያን ጎን እንደሚቆምም አረጋግጠዋል።
የጋራ ደኅንነትን፣ መረጋጋትን እና ብልጽግናን ማሳደግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን የጠቀሱት ኦባሳንጆ፣ ግጭቶችን እና አድልዎዎችን ማስወገድ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የተጠናቀቀው ሀገራዊ ምክክር ለመልካም አስተዳደር ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ "እኛ ከእናንተ ጋር ነን፣ ከጎናችሁ እንቆማለን" ብለዋል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: