Search

አፍሪካውያን የሚሳሱላት ኢትዮጵያ እና የቁጭት ጥሪያቸው

ረቡዕ ነሐሴ 20, 2018 22

አንዳንድ ጊዜ የገዛ ራሳችንን ታላቅነት፣ በረከት እና ክብር አዘውትረን ስለምናየው ብቻ ልንዘነጋው እንችላለን።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ያደረጉት ጥልቅ ንግግር፣ የብዙዎቻችንን ልብ የነካው እና ሕሊናችንን የሞገተው ለዚህ ነው።

ንግግራቸው "እኛ ኢትዮጵያውያን በእርግጥ እናት ሀገራችንን ምን ያህል እናውቃታለን? ምን ያህሉንስ ይገባናል?" የሚል ከባድ የቁጭት እና የመነሣሣት ስሜት ያጫረ ታሪካዊ መልዕክት ነው።

ፕሬዚዳንት ኬንያታ ይህች ምድር ዘመናዊት ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ መላው አፍሪካ እንደ ኩራቱ የሚያያት የጥንታዊ ሥልጣኔ ማዕከል መሆኗን በግልጽ አስገንዝበውናል።

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን የነጻነት፣ የክብር እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የዘላለም ተምሳሌት መሆኗን በስሜት መስክረዋል።

1888 . በዓድዋ ተራሮች ላይ የተካሄደው የነጻነት ተጋድሎ የኢትዮጵያውያን የጦር ሜዳ ድል ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብን ዕጣ ፈንታ የለወጠ እና የአውሮፓውያንን የአይሸነፌነት ትርክት ከመሠረቱ ያናጋ ክስተት እንደነበር አብራርተዋል። ዓድዋ የኢትዮጵያ ልጆች በደም ትሥሥር በአንድነት ቆመው ያመጡት የጋራ ገድል ነው።

አጼ ኃይለ ሥላሴ ቀዳማዊ በዓለም መንግሥታት ማኅበር መድረክ ላይ ያሰሙት ታሪካዊ የፍትሕ ጥሪ፣ እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመመሥረት ኢትዮጵያ የተጫወተችው ዐቢይ ሚና ኢትዮጵያን ለመላው አፍሪካውያን የነጻነት ድምፅ እና የማንነታቸው መመኪያ አድርጓታል።

የአፍሪካውያን ለኢትዮጵያ ያላቸው ዕይታ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳየው ሌላው አስገራሚ ታሪክ ኡሁሩ ስለ አባታቸው ስለ ጆሞ ኬንያታ ያወሱት ትውስታ ነው።

ጆሞ ኬንያታ 1923 . በለንደን ከተማ ወጣት ተማሪ በነበሩበት ዘመን የራሳቸው ሀገር ኬንያ በቅኝ ግዛት ሥር ስለነበረች የነጻነት ባንዲራ አልነበራትም።

በዚህ ጊዜ እኚህ ወጣት አፍሪካዊ የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በክፍላቸው ግድግዳ ላይ በመስቀል፣ ጥቁር ሕዝብ በራሱ መቆም እንደሚችል እንደ ብሩህ ተስፋ ይመለከቱት ነበር።

ይህ አጋጣሚ መላው አፍሪካውያን ኢትዮጵያን የነጻነት አክሊላቸው አድርገው እንደሚወዷት እና እንደሚሳሱላት የሚያሳይ፣ ተስፋ እና ቁጭትን የሚፈጥር ሕያው ምስክርነት ነው።

ከዚህ ታሪካዊ እውነታ ባሻገር ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊነት እና የሕዝቦቿን ውበት እጅግ ማራኪ በሆነ መንገድ አብራርተውታል።

የኢትዮጵያ ውበት ያለው በአንድነት ውስጥ ባለው ልዩነት ነው። ጥንታዊው የአክሱም ንግድ እና ሥልጣኔ፣ ከአንድ ድንጋይ የተፈለፈሉት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አስደናቂ የሕንፃ ጥበብ፣ የሐረር ጀጎል አኩሪ ኢስላማዊ ውርስ፣ እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝብ ያበረከተው ታላቁ የገዳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የእዚህች ድንቅ ምድር የማይነጠፉ የሥልጣኔ ዐሻራዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ማራኪ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ወጎች እና እምነቶች የተሰፋች፣ ውበቷ ዐይን የሚማርክ የጥልፍ ልብስ ናት። አንዱን ክር ብንተረትረው ሙሉ ልብሱ ውበቱን እንደሚያጣ ሁሉ አንዱ ማንነታችን ሲነካ ሌላው ይጎዳል።

ሆኖም ይህን ሁሉ የከበረ ታሪክ የሌሎች አፍሪካውያንን ክብር እና ምስክርነት ስንሰማ "እኛ ኢትዮጵያውያን አፍሪካውያን የሚያውቋትን፣ የሚመኩባትን እና የሚሳሱላትን ያህል ለጋራ እናት ሀገራችን ታማኝ ሆነናልን?" የሚል ከባድ ሕሊናዊ ቁጭት ይፈጥርብናል።

ኢትዮጵያ እጅግ ማራኪ በሆነ መልክዓ ምድር፣ በልዩ አየር ንብረቷ፣ በሰፊ እና ለም የእርሻ መሬት፣ በቡና ጸጋ እና በብዝኃ ሕይወት የተንበሸበሸች ምድር ናት።

አፍሪካውያን ምግባችንን እንድንሰጣቸው ሲጠብቁን እኛ ግን ከጥንካሬያችን ይልቅ ልዩነታችንን በማስፋት፣ የሰላም እና የአንድነት ክራችንን በማላላት ለዘመናት ለድህነት እና ለእንግልት ራሳችንን አሳልፈን ሰጥተናል።

በውስጣችን በፈጠርነው ፖለቲካዊ አለመግባባት የብዝኃነታችንን ጸጋ ከማክበር ይልቅ እርስ በእርስ በመጎተት ራሳችንን አቁስለናል።

ሰብሎቻችን ማሳ ላይ ሳይሰበሰቡ ቀርተዋል፣ ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል፣ ማኅበራዊ ትሥሥራችንም ተፈትኗል።

የፖለቲካ ልዩነቶችን በሠለጠነ የውይይት ጠረጴዛ ላይ መፍታት ሲገባን ወደ ግጭት በማምራታችን፣ ዓለም በኩራት የምትመለከታት ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች ሰላም ሰጥታ መመገብ እስከምትቸገር ደርሳ ነበር። ይህ እጅግ የሚያሳዝን እና ዛሬውኑ ሊቀለበስ የሚገባው የታሪካችን ትልቅ ስብራት ነው።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሁን ከእንቅልፏ ነቅታ ወደሚመጥናት ልዕልና ለመመለስ አዲስ የብርሃን መንገድ መጀመሯን ይህ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በግልጽ አሳይቶናል።

ኡሁሩ ኬንያታ በአጽንኦት እንዳስገነዘቡት፣ ግጭትም ሆነ አለመግባባት በየትኛውም የዓለም ክፍል ሊከሰት ይችላል፤ ነገር ግን እውነተኛው ቤተሰብነት የሚረጋገጠው ከግጭት በኋላ ተመልሶ "የጋራ ቤት" እንዳለን በማስታወስ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን በመፍታት ነው።

የኢትዮጵያ ልጆች ከየአቅጣጫው ተሰባስበው ላለፉት ቀናት ለትውልድ ዐደራ ያስቀመጡበት ሀገራዊ ምክክር ወደዚሁ የጋራ ቤት የመመለሻ እና የታላቅነታችን መነሻ ቁልፍ ነው።

ችግሮቿን በራሷ ልጆች ጥበብ፣ ትዕግሥት እና አስተዋይነት ለመፍታት ቆርጣ የተነሣችው ኢትዮጵያ ይህን የምክክር መድረክ ወደ ቀድሞ ክብሯ የመመለሻ፣ የተፈጥሮ ጸጋዎቿን አልምታ ምጣኔ ሀብቷን የማጠናከሪያ እና ዳግም የአፍሪካውያን የብርሃን ማማ ሆና የምትቀጥልበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ታደርገዋለች።

ኡሁሩ በንግግራቸው ማሳረጊያ እንዳሉት ፈጣን ጉዞ ካስፈለገን ለብቻችን መሄድ እንችላለን፤ ነገር ግን ሩቅ እና አስተማማኝ ጉዞ ከፈለግን በአንድነት አብረን መጓዝ ብቸኛው መንገዳችን ነው።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: