የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ የጦር ሳይንስ እና በከፍተኛ የወታደራዊ ምህንድስና ጥበብ በመታጠቅ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር በማንኛውም ሁኔታ ለማስጠበቅ የሚያስችል የማይበገር አገራዊ አቅም መገንባቱን በግልጽ እያስመሰከረ ይገኛል።
የኢትዮጵያን ጠላቶች አቅመ-ቢስ የሚያደርገው እና ስልታዊ ብልጫን የሚያረጋግጠው ይህ የላቀ የወታደራዊ ምህንድስና አቅም፣ በሳይንሳዊ እውቀት የዳበረ የሰው ኃይል በማፍራት፣ የጦር መሳሪያዎችንና የከባድ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ቴክኖሎጂ በሀገር በቀል መሃንዲሶች በማደስና በማዘመን አስገራሚ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
በአዲስ አበባ እንጦጦ አካባቢ በ1934 ዓ.ም ከተመሰረተበት ታሪካዊ መነሻ ተነስቶ ዛሬ ላይ የመከላከያ ትምህርት እና ሥልጠና ዋና መምሪያ አካል የሆነው የመከላከያ ውጊያ ምህንድስና ኮሌጅ፣ ከመሰረታዊ ሙያ እስከ መጀመሪያ ዲግሪ በሚሰጣቸው ዘመናዊ የትምህርት መስኮች ሀገርን በብቃት የሚጠብቅና ጠላትን የሚያስከዳ አስተማማኝ አቅም እየገነባ ይገኛል።
በተለይም የመከላከያ አዋጅ ቁጥር 1286/2015 ጸድቆ ወደ ተግባር መግባቱን ተከትሎ ከተካሄደው ጥልቅ ተቋማዊ ሪፎርም በኋላ፣ ምህንድስና ከምድር፣ ከአየር፣ ከባሕር እና ከሳይበር ኃይሎች ጎን ለጎን ራሱን የቻለ ቁልፍ ተቋማዊ ምሰሶ ሆኖ መደራጀቱ የሠራዊቱን የውጊያ ዝግጁነት እና የግዳጅ ፈጣንነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
በቢሾፍቱ የመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ የዝግጁነት ወርክሾፕ ማዕከል የቀደሙ ከባድ የጦር ተሽከርካሪዎች፣ የሮኬትና የሚሳኤል ሥርዓቶች በሀገር በቀል ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ታድሰው ወደ ሙሉ ውጊያ ዝግጁነት እንዲመለሱ መደረጉ፣ የሀገር ውስጥ አቅምን በማጎልበት የጠላትን አላስፈላጊ ተስፋ የሚያክስና ለውጭ ምንዛሬ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ሀብት የታደገ ታላቅ ድል ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ምህንድስና በውጊያ ቀጣናዎች የጠላትን ግስጋሴ የሚገቱ ስልታዊ እንቅፋቶችን በመገንባትና የሠራዊቱን ሞቢሊቲ በማረጋገጥ ረገድ ከሚያሳየው ፍጹም የበላይነት ባሻገር፣ በሰላም ጊዜ ለብሔራዊ ልማት የሚውል ግዙፍ አቅም መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያስፈልጉ ከባድ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ ይወስድ የነበረውን የ14 ቀናት አድካሚ ጉዞ ወደ 1 ቀን ዝቅ ያደረገው የ210 ኪሎ ሜትር የግልገል በለስ እና የአባይ ግድብ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት፣ የተቋሙን ወደር የሌለው የፅናት እና የብቃት ከፍታ የሚያረጋግጥ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ የሠራዊቱን አባላት የኑሮ ደረጃ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የሕክምና እና የደመወዝ ሁኔታ ያሻሻለው ዘመናዊ አደረጃጀት፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን በሰላም ጊዜ ለልማት፣ በፈተና ጊዜ ደግሞ ለድንገተኛ ክስተት የማትበገርና የጠላቶቿን ሴራ ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ የምትችል ጽኑ ሀገር አድርጓታል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: