Search

የሰሜን ዋልታ የሀብት ጦርነት የአርክቲክ መቅለጥ የፈጠረው የብሪክስ እና የኔቶ አዲስ የጂኦፖለቲካ ፍጥጫ

ረቡዕ ነሐሴ 20, 2018 42

ለአያሌ ዘመናት በበረዶ ተሸፍኖ እና ከሰው ልጅ ተደራሽነት ተሰውሮ የነበረው እጅግ ቀዝቃዛው የአርክቲክ ቀጠና፣ በአሁኑ ወቅት የዓለም ልዕለ-ኃያላን ሀገራት የኃይል ማሳያና የጂኦፖለቲካ ፍጥጫ ማዕከል ሆኗል።

አየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ተፅዕኖ የአርክቲክ ግግር በረዶ ከሌላው የዓለም ክፍል በሦስት እጥፍ በሚበልጥ ፍጥነት እየቀለጠ መምጣቱ፣ ለዘመናት ተቆልፈው የነበሩ አዳዲስ የባህር ንግድ መስመሮችንና ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብቶችን በቀላሉ ለማግኘት መንገድ ከፍቷል።

ይህ አዲስ ሁኔታ የቀደመውን የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ እና የጉዞ ጊዜ በእጅጉ እየቀየረው ሲሆን፣ ለአብነትም የደቡብ ኮሪያ የንግድ መርከብ በባህላዊው የስዊዝ ቦይ መስመር አውሮፓ ለመድረስ እስከ 80 ቀናት ይወስድባት የነበረውን ጉዞ በአዲሱ የአርክቲክ መስመር ወደ 40 ቀናት በማሳነስ ወጪና ጊዜዋን በግማሽ መቀነስ ችላለች።

በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ እና በቀይ ባህር አካባቢ በሚስተዋሉ የጂኦፖለቲካ ፍጥጫዎች ሳቢያ መደበኛ የንግድ መስመሮች ስጋት ውስጥ በመውደዳቸው፣ ዓለም አርክቲክን እንደ ዋነኛ የንግድ አማራጭ እንድታማትር አስገድዷታል።

ከዚሁ የአርክቲክ ግግር በረዶ ስር የተሸሸገው ያልተነካ ግዙፍ የኢኮኖሚ ሀብት የኃያላኑን ፉክክር ይበልጥ አጋግሎታል።

በአርክቲክ ውቅያኖስ ስር 13 በመቶ ያልተነካ የዓለም የነዳጅ ክምችት፣ 30 በመቶ የተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም ውድ ማዕድናት የሚገኙ ሲሆን፣ እንደ ኖርዌይ ያሉ ሀገራት በአካባቢው የነዳጅ ቁፋሮአቸውን በስፋት እያከናወኑ ይገኛሉ።

ይህ ግዙፍ ሀብት በቀጠናው ላይ ከፍተኛ የወታደራዊና የደህንነት ስጋት የደቀነ ሲሆን፣ የብሪክስ አባል የሆነችው ሩሲያ ወታደራዊ ጣቢያዎቿን በማደስና አዳዲስ የኑክሌር መርከቦችን በመገንባት የበላይነቷን ለማረጋገጥ እየጣረች ነው።

ቻይናም በበኩሏ "የፖላር ሀር መንገድ" የሚል አዲስ የባህር መስመር በመቅረጽ መዋዕለ ነዋይ እያፈሰሰች ትገኛለች።

በተቃራኒው ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን መቀላቀላቸውን ተከትሎ የምዕራባውያን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ በመጨመሩ የአካባቢው ውጥረት እየጋለ መጥቷል።

የአርክቲክ ግግር በረዶ መቅለጥ የቀጠናውን የተፈጥሮ ገጽታ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉን የጂኦፖለቲካና የኢኮኖሚ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረው ይገኛል።

የሰሜን ዋልታ ከአካባቢ ጥበቃ አጀንዳነቱ አልፎ፣ የዓለም ልዕለ-ኃያላን ሀገራት ያልተነካ የኃይል ሀብት የሚቀራመሙበትና ወታደራዊ አቅማቸውን የሚያንፀባርቁበት አዲስ የአለም አቀፍ ፖለቲካ ግንባር ሆኖ ቀጥሏል።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: