Search

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የተገነቡ አራት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች እና ተርሚናሎችን መርቀው ሥራ አስጀመሩ

ረቡዕ ነሐሴ 20, 2018 44

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጎተራ፣ ቦሌ፣ የካ እና ቀበና የተገነቡ አራት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን፣ ተርሚናሎችን እና የገበያ ማዕከላትን መርቆ አገልግሎት ማስጀመሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ከንቲባዋ ይህንኑ አስመልክቶ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ እነዚህ አዳዲስ መሠረተ ልማቶች የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ የሚያቃልሉ እና የትራንስፖርት ሥርዓቱን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቶቹ ሕዝቡን ከዝናብ እና ከፀሐይ እንግልት በመጠበቅ የሰውን ክብር የሚመጥን ምቹ እና ንፁህ አገልግሎት እንደሚሰጡ እንዲሁም በርካታ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ አብራርተዋል።

እነዚህ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች በአንድ ጊዜ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ማቆሚያዎችን፣ የታክሲ እና የአውቶቡስ ተርሚናሎችን፣ የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያዎችን፣ ሰፊ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን፣ የንግድ ሱቆችን እንዲሁም ካፍቴሪያዎችን እና ሬስቶራንቶችን ያካተቱ ናቸው።

ከዚህም ባለፈ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ምቹ የተሳፋሪ መጠበቂያዎች፣ የትኬት መቁረጫ ቴክኖሎጂዎች፣ አሳንሰሮች፣ ንፁህ መፀዳጃ ቤቶች፣ የደኅንነት እና የአደጋ ቅድመ መከላከል ሥርዓቶች የተሟሉላቸው በመሆኑ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

ከንቲባዋ እንዳስታወቁት፣ ከለውጡ በፊት በአዲስ አበባ የአንድ ጊዜ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አቅም ሦስት ሺህ ብቻ የነበረ ሲሆን ምንም ዓይነት ተርሚናል አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ግን አስተዳደሩ በጥራት እና በፍጥነት ባከናወናቸው ግንባታዎች የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን እና ተርሚናሎችን የመያዝ አቅም 170 ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

አስተዳደሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የገባውን ቃል በተግባር እየፈጸመ መሆኑን ያረጋገጡት ከንቲባ አዳነች፣ አዲስ አበባ ከዚህ በላይ እንደሚገባት በማንሣት በቀጣይም ከዚህ በበለጠ በትጋት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

ፕሮጀክቶቹ ዕውን እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ የዲዛይን እና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ እና የትራንስፖርት ቢሮ አመራሮች እና ሠራተኞች፣ እንዲሁም ለኮንትራክተሮች፣ ለአማካሪዎች እና በሥራው ለተሳተፉ አካላት በሙሉ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: