በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ተመካካሪዎች፣ ለሀገራችን ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦች አጠናቅረው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማስረከባቸውን የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረ ሥላሴ አስታወቁ።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት፣ በምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በቀላሉ መግባባት የቻሉ ሲሆን፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ደግሞ ሰፊ ጊዜ ወስደው ጠንከር ያሉ ውይይቶችን እና ክርክሮችን በማድረግ በመጨረሻ ላይ በአብዛኛዎቹ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ችለዋል።
ኮሚሽኑ አጠቃላይ ሂደቱን በቅርበት ሲከታተል እንደነበር እና የምክክር መድረኮቹ በመደማመጥ፣ በመከባበር እና በመቻቻል መንፈስ መከናወናቸውን ማረጋገጡን ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ የሐሳብ ልዩነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ተወያይተው የጋራ መግባባት በመፍጠር በጋራ ወደፊት መራመድ የሚችሉበትን ዕድል ማመቻቸት መሆኑን ያነሡት ወይዘሮ ሂሩት፣ "ሀገራዊ ምክክር አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚለይበት ሂደት ወይም አንዱ ወገን አሸንፎ ሌላው የሚሸነፍበት ውድድር አይደለም" በማለት የምክክሩን መሠረታዊ መርሕ በአጽንኦት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከምክረ ሐሳቦች እና ከስምምነቶችም ባሻገር ሌሎች ዘላቂ ውጤቶችን ማስገኘቱ በመግለጫው ተነሥቷል። በዚህም ተመካካሪዎች እርስ በርስ መተዋወቃቸውን፣ ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነቶች መፍጠራቸውን፣ የተለያየ አመለካከቶችን ማዳመጣቸውን እንዲሁም በሀገራችን ፈተናዎች ላይ ሰፊ ሐሳብ ተለዋውጠው መግባባት ላይ መድረሳቸውን ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አብራርተዋል።
ይህ ሂደት በኢትዮጵያ የምክክር ባህልን ለመገንባት ትልቅ መሠረት የጣለ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሂሩት፣ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያሉባትን የሐሳብ ልዩነቶች በውይይት እና በምክክር መፍታት እንደምትችል በተግባር ያሳየችበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን አመላክተዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለጉባኤው መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል።
በተለይም ኢትዮጵያውያን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እርስ በርስ ለመደማመጥ፣ ልዩነቶችን አክብረው ለመመካከር እና የመግባቢያ ነጥቦችን በጋራ ለመፈለግ ላሳዩት ከፍተኛ ቁርጠኝነት ኮሚሽኑ ታላቅ አድናቆቱን ገልጿል።
የዚህ ሂደት ስኬት በብዙ ጉዳዮች ላይ የመግባባት መሠረት መጣሉ መሆኑንም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለው በመግለጽ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዮናስ በድሉ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: