የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሂደቱ የዜጎችን የመከባበር፣ የመመካከርና የመደማመጥ ባህል ያረጋገጠ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ገለጹ።
ከንቲባዋ፣ "ከአሸናፊ-ተሸናፊ ትርክት በመላቀቅ፣ በሀሳብ ልዕልና ወደ በጋራ የማሸነፍ፣ ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል የጋራ መፍትሔ ለማምጣት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ወደ መግባባት የተሸጋገርንበት ታላቅ የታሪክ እጥፋት ነው" ብለዋል።
እንዲመከሩባቸው ከቀረቡት 400 ዐበይት ጉዳዮች ውስጥ ተሳታፊዎች ተደማምጠው እና አንዱ የሌላውን ህመም ተረድተው በ99 በመቶዎቹ ላይ ሙሉ ስምምነት ላይ መድረስ መቻሉን ገለልጸዋል።
"በዚህ የምክክር ሂደት የተለየ አሸናፊና ተሸናፊ ፈጽሞ አልተፈጠረም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያ አሸንፋለች" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ውሳኔ ያልተደረሰባቸው 1 በመቶ ጉዳዮችም በአማራጭ መፍትሄዎች እንዲታለፉ በሙሉ መግባባት ላይ መደረሱን አክለዋል።
ይህ ዓይነቱ አካሄድ እስካሁን በዓለም ላይ ከታዩ የምክክር ሂደቶች እጅጉን በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፣ ያለፉት ትውልዶች በጽኑ ተመኝተውት ያላዩትን ይህን የሰለጠነ አብሮነት ያሳካው የአሁኑ ትውልድ እጅግ የታደለ መሆኑንም በመልዕክታቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የምትጸናውም አንዱ የሌላውን ሀሳብ ለማዳመጥና ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆን በሚገነባ የሰለጠነ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዛሬ ተግባባን ማለት ነገ ምንም አይነት ልዩነት አያጋጥመንም ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ነገር ግን "ልዩነትን በመመካከር እና በሰለጠነ መንገድ መፍታት ተጀምሯል፤ በሩም ተከፍቷል፤ ከእንግዲህ ወደ ኋላ አንመለስም" ብለዋል።
አክለውም፣ "ከእንግዲህ ልጆቻችን ልዩነቶቻቸውን በጠመንጃ ለመፍታት በመሞከር እና እርስ በእርስ በመገዳደል አይቀጥሉም። ይህ የጦርነት እዳ ወደ እነሱ እንደማይተላለፍ እምነት አለን" ብለዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: