የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባለፉት 46 ቀናት አራት ሺህ ተመካካሪዎችን ያቀፈና በስኬት ያጠናቀቀው ታሪካዊ የምክክር ጉባኤ፣ ኢትዮጵያውያን የሐሳብ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ ሀገራዊ ራዕይ ላይ ለመምከር በአንድነት የቆሙበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ አስመዝግቧል።
በእነዚህ ቀናት የተንጸባረቀው ዋነኛ እውነት “የእኔ” ከሚል ጠባብ የቡድንና የግል አስተሳሰብ ወጥቶ “የእኛ” ወደሚል ሰፊና አጠቃላይ ሀገራዊ ራዕይ መሸጋገር መቻሉ ነው።
ተመካካሪዎቹ በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በሚመክሩበት ወቅት የየራሳቸውን እይታ ይዘው ቢቀርቡም፣ የውይይቱ ማጠቃለያ ግን የአንድ የጋራ ቤት ግንባታ ላይ ያተኮረ በመሆኑ በኢትዮጵያ የምክክር ባህል ውስጥ ትልቅ የለውጥ ምዕራፍን ያመላከተ ሆኗል።
ይህ አህጉራዊና ሀገራዊ ትኩረትን የሳበ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያውያን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር መዋደድና መቀራረብ ምን እንደሆነ በተግባር ያሳዩበት፣ ልዩነቶችንም በኃይል ወይም በእልህ ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ፣ በመደማመጥና በመከባበር የመፍታት አቅም እንዳላቸው ያረጋገጡበት መድረክ ነበር።
በልዩ ልዩ ምክንያት ተራርቀው የቆዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጽኑ መደጋገፍና በመተማመን የተሰበረውን የማህበራዊ ድልድይ ጠግነው አዲስ የእርቅና የቃል ኪዳን መስመር የዘረጉ ሲሆን፣ ይህ የምክክር መድረክ የመጨረሻ ግብ ሳይሆን የረጅም ጉዞ መጀመሪያ መሆኑ ተመልክቷል።
አራት ሺህ ተመካካሪዎች ያነሷቸው አጀንዳዎችና የደረሱባቸው የጋራ መግባባቶች ሀገራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሰረቶች በመሆናቸው፣ አሁን የሚጠበቀው በእነዚህ 46 ቀናት የተገነባውን “የእኛነት” መንፈስ ወደ ተግባር በመቀየር ጠንካራና የተረጋጋች ሀገር የመገንባት ኃላፊነትን በጋራ መወጣት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: