የጽናት፣ የጀግንነትና የሀገራዊ ድል ውጊያ አቅጣጫ ቀያሪው የኢትዮጵያ አየር ወለድና ኮማንዶ ኃይል ሀገራዊ አደራውን በላቀ ቆራጥነት መወጣቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
በሀገር ሉዓላዊነት፣ ክብርና ደኅንነት ማስከበር ታሪክ ውስጥ የታሪክን አቅጣጫ የመቀየርና በውጊያ መስክ ላይ የሚወሰን ወሳኝ ድል የመጎናጸፍ ልዩ ስትራቴጂካዊ አቅም ያለው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት አምበል የሆነው የአየር ወለድ እና ኮማንዶ ኃይል፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ታላቅ አደራ አንግቦ በመንቀሳቀስ የሀገር መከታነቱንና የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር አስመስክሯል።
በከፍተኛ ወታደራዊ ሳይንስ፣ በእናት ሀገር ፍቅርና በጽኑ ዲሲፕሊን የተቀረፀው ይህ ልዩ ኃይል፣ በተላበሰው የላቀ የውጊያ ጥበብና ፈጣን የስምሪት ስልት ከባድ አደጋዎች በሚደቀኑበት ቅጽበት በጠላት ላይ ያልተጠበቀ ድንገተኛ ምት በማሳረፍ፣ የተቃጣን አደጋ በአጭር ጊዜ በማክሸፍ የውጊያውን ሚዛን ወዲያውኑ ወደ አጠቃላይ ሀገራዊ ድል የመቀየር ልዩ ችሎታ ያለው ኃይል ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከውስጥና ከውጭ የተቃጡባትን ወረራዎችና ግጭቶች በምትመክትበት ወቅት፣ ይህ ልዩ ኃይል የመከላከያ ሠራዊቱን ግንባር ቀደም አቅም በመሆን በተራራማ፣ በበረሃማና በከባድ የአየር ንብረት ውስጥ ሳይበገር፣ ወጣ ገባና አስቸጋሪ መሬቶችን ለጠላት ወጥመድ፣ ለራሱ ደግሞ የውጊያ ዕድል በማድረግ ሀገራዊ አደራውን በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል።
የሀገርን የድንበር ወሰንና ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ የሀገር ውስጥ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚደቀኑ ስጋቶችን በፍጥነት በማስወገድ ረገድ ወሳኝ ሚና ያለው ይህ የጀግንነት ማሳያ የሆነ ኃይል፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ አደራ ታማኝ በመሆን ስሙን በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቅ ቀለም መጻፉን አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: