ለዘመናት የሕዝብን ሕመም ተሸክመው፣ ሕይወትን በሕክምና ታድገው በርካታ ትውልዶችን ሲያገለግሉ የቆዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ዛሬ ሁለንተናዊ መታደስና ዘመናዊነትን ተላብሰዋል።
ከጊዜ ብዛት ያረጁ ሕንፃዎች፣ ጊዜ ያለፈባቸው የመሣሪያዎች እጥረትና መጨናነቅ የትናንት ገጽታቸው የነበረ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የጤና ዘርፍ ማሻሻያ አዳዲስ ሕንፃዎች፣ የላቁ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችና የተቀላጠፈ የአገልግሎት ስሪት ተተክተዋል።
የዚህ ታሪካዊ ለውጥ ህያው ማሳያ የሆነው የራስ ደስታ ሆስፒታል በግቢው ውስጥ በተገነባው ባለ ሰባት ወለል ዘመናዊ ማዕከል፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ኤምአርአይ፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ፣ ተንቀሳቃሽ ኤክስሬይ እና በሰዓት 30 ሺህ ሊትር ኦክስጅን የሚያመርት ፕላንት ተገጥሞለታል።
በተጨማሪም ለሕክምና ባለሙያዎች የተዘጋጁ ቤተ-መጻሕፍት፣ ዘመናዊ ቢሮዎች፣ የስብሰባ አዳራሾችና ካፌቴሪያዎች የሥራ አካባቢውን ምቹ አድርገውታል።
ይህ የጤና ዘርፍ እድገት በአንድ ተቋም ብቻ ሳይወሰን፣ የኢትዮጵያን የምርመራ አቅም ወደ አዲስ ደረጃ ያሸጋገረው የዘረመል (DNA)፣ የፎሬንሲክና የሥነ-ምርዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል እንዲሁም በቅርቡ የተገነባው ላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዚሁ ዘመናዊነት አካል ሆነዋል።
ላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተለይም የካንሰርና የልብ ሕክምናዎችን የሚያግዙ የላቁ ቴክኖሎጂዎች፣ በሰዓት 80 ሜትሪክ ኪዩብ ኦክስጅን የሚያመርት ፕላንት እና ባክቴሪያን የሚቋቋሙ ንጣፎች የተገጠሙለት ነው።
ሆስፒታሎችን ማደስ ማለት አዲስ ሕንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን በታካሚዎች ላይ ተስፋን ማደስ፣ ለሐኪሞች የተሻለ ከባቢ መፍጠርና ዜጎች ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱበትን ወጪ በማስቀረት ሀገራዊ አቅምን ማሳደግ በመሆኑ፣ ቀደም ሲል በአሮጌ ሕንፃዎች ውስጥ ይደረግ የነበረው ትልቅ አገልግሎት ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የላቀ አገልግሎት መስጫ ሆኗል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: