ለዘመናት በፖለቲካ አዙሪት፣ በታሪካዊ ቅራኔዎችና በግጭት ስትናጥ የኖረችው ታሪካዊቷ ምድር ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በገዛ ልጆቿ የውይይት ብዕርና የምክክር ጥበብ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጽፋለች።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያከናወናቸው አካታች፣ ተከታታይ እና አድካሚ የውይይት መድረኮች ኢትዮጵያን ወደ ሌላ ብሩህ ምዕራፍ አሸጋግረዋታል።
ይህም ዘላቂ ሰላምና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ የተወሰደ ታሪካዊ እጥፋት ሆኖ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው የውጭ ወራሪዎችን በመመከት ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት እንደሆኑ ሁሉ፣ ዛሬም ውስብስብ የሆኑ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልዩነቶቻቸውን በኃይል ሳይሆን በሰለጠነ ውይይት፣ በመደማመጥና በመግባባት መፍታት እንደሚችሉ ለአፍሪካና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስመስክረዋል።
ይህ አጋጣሚ ቁስል በውይይት የሻረበት፣ ልዩነት በመከባበር የላላበት እና የኃይል ፖለቲካ ያከተመበት ታሪካዊ ክስተት ነው።
የጥቂት ልሂቃንን የጥቅም ድርድርና የዝግ በር ልማዶችን የቀየረው ይህ ሂደት፣ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል የተወከሉ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን፣ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በማሳተፍ የ130 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ድምፅ አድምጧል።
የመደመር መንግስት ባቀረበው ጥሪ ተፎካካሪዎች ከታጣቂነት ወደ ፖለቲካዊ አማራጭ በመሸጋገር ቅራኔዎቻቸውን በሀሳብ አደባባይ እንዲፈቱ አድርጓል።
የምክክሩ ስኬት የሀገር ሀብትና እውቀት ወደ ምርታማነት፣ ኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማት እንዲዞር ሁኔታዎችን የሚያመቻች ሲሆን፣ በምስራቅ አፍሪካም የውስጥ መረጋጋቷን በማጠናከር በቀጠናው ሰላምና ዲፕሎማሲ ላይ ንቁ ሚናዋን እንድትወጣ ያደርጋል።
የምክክሩ መጠናቀቅ የተገኙ መግባባቶችን ወደ ተጨባጭ ተግባር የመቀየር አዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ በመሆኑ፣ የዛሬው የጋራ መግባባት ሀገራችንን ወደ ሁለንተናዊ ልማትና ጠንካራ አንድነት የሚያሸጋግር ህያው ተስፋ ሆኗል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: