ኢትዮጵያ ያላትን ዘለቄታዊ ሰላምና ሕብረት ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት እንዲሁም የሕዝቦቿ አብሮ የመኖር እሴት፣ ሀገርን አጣብቆ የሚይዝ ዋና የእድገትና የመደጋገፍ ሞተር መሆን እንደሚችል በሀገራዊ ምክክሩ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የቀድሞው የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ገለጹ።
በሀገራዊ ምክክሩ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቀድሞው ፕሬዚዳንቱ፣ ከአህጉራችን አፍሪካ ውጭ ያሉ አካላት የኢትዮጵያን ብዝኃነት እንደ ድክመት በመቁጠር የሕብረቷን ምስል ተሰባብሮ ለማየት ቢመኙም፣ ኢትዮጵያውያን ግን “የሸረሪት ድር ከተባበረ አንበሳን ያስራል” የሚለውን ጥንታዊ ምሳሌያዊ አነጋገር በመከተል የጽናታቸውን ጥንካሬ ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ ሕዝቦች ባህላዊ ሀብት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በአንድ ክልል፣ በአንድ ቋንቋ፣ በአንድ እምነት ወይም በአንድ የፖለቲካ መስመር ብቻ ተገድባ የምትብራራ ሀገር ሳትሆን፣ ታላቅነቷ በተለያዩ ቀለማት ክሮች የተሸመነ ሕብረ-ቀለም መሆኑን አብራርተዋል።
ልክ በአንድ ቀለም ብቻ የተሸመነ ምንጣፍ ህይወትና ውበት እንደሚያጣ ሁሉ፣ የኢትዮጵያም ውበት የሚመጣው ከተለያዩ ባህሎች ውህደትና መከባበር እንደሆነ ያነሱት ኡሁሩ ኬኒያታ፣ ብዝኃነቷ እንደ ፖለቲካ ችግር ሳይሆን እጅግ ድንቅና የማይተካ ብሔራዊ ሀብት እንደሆነ አስምረውበታል።
ምንም እንኳን አስተዳደራዊ ወሰኖች ቢኖሩም መንገዶች፣ ወንዞች፣ ንግድ፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶችና ታሪክ ሁሉንም ማህበረሰቦች አቋርጠው እንደሚያገናኙ በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ የሁሉንም ሕዝቦቿን እኩል ተሳትፎና ድምፅ የምትፈልግ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
በታሪክ አጋጣሚዎች በተከሰቱ ግጭቶች ከባድ ዋጋ ቢከፈልም፣ ከግጭት በኋላ አንድ የጋራ ቤት እንዳላቸው ማስታወሳቸው የቤተሰብነታቸው ማረጋገጫ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን የጋራ እጣ ፈንታቸውን በማሰብ በሰላምና በውይይት አንድነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: