ትምህርት የኢትዮጵያ የኅልውና እና የዕድገት መሰረት ነው፡፡ ጠንካራ እና በራሷ አቅም የምትተማመን ኢትዮጵያን ለመገንባት መነሻው ዛሬ ላይ ሆነን የምንቀርጸው ትውልድ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በባዶ ሆድ የሚማር ልጅ አዕምሮው ዕውቀት ሊቀስም አይችልም፡፡ ነገንም በተስፋ ለመመልከት ይቸገራል፡፡ እዚህ ላይ ነው የተማሪዎች ምገባ እና የትምህርት ቤቶች ማዘመን ትርጉም በጉልህ የሚታየው፡፡
ይህ ጉዳይ ከመንግሥት ፖሊሲነት ባለፈ በእያንዳንዱ ወላጅ ጓዳ ውስጥ ያለውን ሕይወት ይነካል፡፡ የትውልድ ታሪክን የሚቀይር ማኅበራዊ ፍትሕንም ያረጋግጣል፡፡
መደመር የሚለውን እሳቤ በፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም መነጽር ብቻ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ነገር ግን መደመር መሬት ወርዶ የሰው ልጅን መሰረታዊ ክብር ሲመልስ የምናየው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡
የሰው ተኮር ልማት እሳቤ ቁንጮ የሆነው የተማሪዎች ምገባ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለምን ወደ ተግባራዊ የሕይወት ለውጥ የቀየረ አስደናቂ ስኬት ነው፡፡
በአንድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ የሀብታምም ሆነ የድሃ ልጅ አንድ ዓይነት የደንብ ልብስ ለብሰው ከአንድ ማዕድ እኩል ይመገባሉ፡፡ ይህም መደመር ክፍተትን ማጥበብ እና የልጆችን የሥነ-ልቦና ስብራት መጠገን መሆኑን ያሳያል፡፡
ይህንን ለውጥ በራሳችሁ ሕይወት ወይም በቅርብ ጎረቤታችሁ ኑሮ ውስጥ አስቡት፡፡ በጠዋት ተነስታ "ልጄ ዛሬ ምን በልቶ ይውላል? ምን ቋጥሬ ወደ ትምህርት ቤት ልላከው? በባዶ ሆዱ እንዴት አዕምሮው ትምህርት ይቀበላል?" እያለች በስጋት የምትጨነቀውን የድሃ እናት ስሜት በህሊናችሁ ሳሉት፡፡
ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ ትምህርት ቤት የሚሄደውን እና በትምህርት ገበታው ላይ እያለ በረሃብ ምክንያት የሚወድቀውን ልጅ እና የመምህራኑን ስሜት አስቡት፡፡
ዛሬ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ አንድ ሚሊዮን ገደማ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ትኩስ እና የተመጣጠነ ምግብ በትምህርት ቤታቸው አግኝተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በክልሎች እና በሀገር በቀል የምገባ ፕሮግራሞች አማካኝነት ከ9.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደብተር፣ መጻፊያ ቁሳቁስ እና የደንብ ልብስ በነጻ ይቀርብላቸዋል፡፡ ይህ ተግባራዊ እርምጃ ለበርካታ ወላጆች የሰጠው የኢኮኖሚ እና የሥነ-ልቦና እፎይታ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡
እናቶች ሸክማቸው ቀልሏል፡፡ ልጆችም በረሃብ አዕምሯቸው ሳይዝል እና በኑሮ ጫና ሳይሸማቀቁ ሙሉ ትኩረታቸውን ትምህርታቸው ላይ ማድረግ ችለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ከትምህርት ገበታ በረሃብ ምክንያት የሚቀሩ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ የትምህርት አቀባበላቸውም በሚያስደንቅ ሁኔታ ተሻሽሏል፡፡ ለዚህም ነው በአዲስ አበባ ብቻ በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ95 በመቶ በላይ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት፡፡
ከምገባው መርሐ ግብር ባሻገር ትምህርት ቤቶችን የማዘመን ሰፊ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ ከ300 በላይ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ እና የመሰረተ ልማት ማሻሻያ ሥራ ተሠርቷል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃም ከ4 ሺህ በላይ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ትምህርት ቤቶች ተሻሽለው ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች፣ ንጹህ የመጸዳጃ ቤቶች፣ ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍት እና የምግብ ማብሰያ አዳራሾች ተገንብተውላቸዋል፡፡
የተስተካከለ እና ንፁሕ አካባቢ ለተማሪዎች የሚሰጠው የክብር ስሜት ከፍተኛ ነው፡፡ እነዚህ ሰው ተኮር ልማቶች ዛሬ ላይ ተማሪውን ከማስደሰት አልፈው ለኢትዮጵያ ዕድገት ወሳኝ መሰረት እየጣሉ ነው፡፡
በተጨማሪም የትምህርት ሚኒስቴር የላቀ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎችን ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ ለማዘጋጀት በየክልሉ የላቀ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ሥራ እየጀመሩ ሲሆን፣ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመንም በርካታ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡
በእነዚህ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎበዝ ተማሪዎች ሙሉ ወጪያቸው በመንግሥት ተሸፍኖ በጥራት እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እየቀሰሙ ይገኛሉ፡፡
በአካል የዳበረ፣ በሥነ-ልቦና ያልተሰበረ፣ በእኩልነት ያደገ እና በዕውቀት የታነጸ ትውልድ ነገ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ እንደሚያሸጋግራት አያጠራጥርም፡፡
የትምህርት ቤት ምገባ፣ የቁሳቁስ ማሟላት፣ የትምህርት ቤቶች ማዘመን እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት የትውልድ ግንባታ የማዕዘን ድንጋዮች ናቸው፡፡
እነዚህ ተጨባጭ ሥራዎች በወረቀት ላይ የነበረን ንድፈ ሐሳብ ወደ መሬት አውርደዋል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥም እውነተኛ የአንድነት መንፈስን እየፈጠሩ ነው፡፡
ዛሬ በትምህርት ገበታቸው ላይ በክብር የተመገቡ እና የተሟላ ቁሳቁስ ያገኙ ህጻናት ነገ ኢትዮጵያን በክብር የሚያስጠሩ ጀግኖች ይሆናሉ፡፡
ይህ ሁላችንም በልጆቻችን ብሩህ ተስፋ ውስጥ የራሳችንን የተሻለ ነገ እንድናይ የሚያደርግ እና ትውልድን በእኩልነት የሚያንጽ እውነተኛ የለውጥ መንገድ ነው፡፡
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: