የፊታችን ማክሰኞ የሚከበረውን 1501ኛውን የነቢዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ልዩ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
"ፍትሃዊ ነቢይ (ሰዐወ) መውሊድ በሀበሻ እና ሁለንተናዊ ፋይዳው" በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ነቢዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) የሰውን ልጅ መልካም ሥነ-ምግባር ለማስተማር የተላኩ፣ የሰላምና የፍትህ ተምሳሌት መሆናቸው ተመላክቷል።
ነቢዩ (ሰዐወ) ከተለያዩ እምነት ተከታዮች ጋር በፍቅር፣ በመከባበር እና በታላቅ ርኅራኄ አብሮ መኖር እንደሚገባ በተግባር ያስተማሩ ታላቅ መሪ መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል።
አሁን ያለው ትውልድ ይህንን የነቢዩን (ሰዐወ) አርዓያነት በመከተል፣ መልካም ስብዕናን በመላበስ ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላምና ለአንድነት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል፡፡
የመውሊድ በዓል የነቢዩን (ሰዐወ) አስተምህሮ ለዓለም ለማስተዋወቅና የእርስ በርስ መረዳጃ መድረክ ሆኖ ለዘመናት ማገልገሉ ተጠቅሷል።
ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት (ሰደቃ በማብላት)፣ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር እና የሀገርን ሰላም በመጠበቅ ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል።
የፓናል ውይይቱ በታላቁ አንዋር መስጂድ ወጣት ጀመዓ እና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ላይ ታዋቂ ኡለማዎች፣ ኢማሞችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
በመሐመድ ራህመቶ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: