በአፍሪካ እና ቀጣናዊ ተፎካካሪነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የጂኦፖለቲክስ ለውጦች ባሉበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የብሔራዊ ኅልውናና የረጅም ጊዜ ልማት መሠረት ሆኖ ቀጥሏል።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባሕር በር በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ብቻ ለመመለስና አስተማማኝ የመውጫ በር ለማግኘት እያደረገች ያለውን ጥረት አጠናክራ ቀጥላለች።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና በአፍሪካ በግንባር ቀደም ከሚጠቀሱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስመዘግቡ ሀገራት አንዷ ብትሆንም፣ ቀጥተኛ የባሕር በር አለመኖሩ በወጪና ገቢ ንግዷ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ በመሆኑ በዓመት ለወደብ አገልግሎት ክፍያ የምታወጣውን ቢሊዮን ዶላሮች ለማስቀረት አስተማማኝና አማራጭ የባሕር መውጫ ማግኘት የትውልድ ጥያቄና የዘላቂ ልማት መሠረት ሆኗል።
ሀገራችን የምትከተለው የዲፕሎማሲ አካሄድ በጋራ ተጠቃሚነት እና በጎረቤት ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላምን በማስፈን መርህ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ጥያቄው የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት ሳይጋፋ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በጋራ ልማት ላይ የተመሠረተ ትስስር ለመፍጠር ያለመ ነው።
የኃይል አማራጭን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ በንግግርና በድርድር ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት እየተከናወነ ያለው ይህ ጥረት፣ የወደብ አማራጮችን ማግኘት የአንድ ሀገር ጥቅም ብቻ አለመሆኑን በማስገንዘብ አጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድን የኢኮኖሚ ትስስርና ሰላም የሚያጠናክር ነው።
ኢትዮጵያ በጎረቤቶቿ መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን በማጠናከርና የጋራ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን በመጋራት የባሕር በር ጥያቄዋን እውን ለማድረግ በጽናት እየሠራች የምትገኝ ሲሆን፣ ይህም የወደፊት የኢኮኖሚ ታላቅነቷን ከመተመኑም በላይ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የትብብርና የጋራ ዕድገት ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: