ማኅበራዊ ፍትህን ማስፈን እና ለዜጎች ሰብዓዊ ክብርን መመለስ የወረቀት ላይ ንድፈ ሐሳብ መሆኑ አብቅቶ በተግባር መሬት የነካበት የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ካደረጓቸው አምስቱ የ"ዜሮ ግቦች" መካከል ዋነኛው የሆነው ተረጂነትን እና ልመናን ዜሮ ማድረግ የተሰኘው እሳቤ የሰዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በተጨባጭ እየቀየረ ነው።
ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከጥገኝነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ይህ ራዕይ በጠንካራ ማኅበራዊ መደጋገፍ ታጅቦ ሰፊ ውጤት ማምጣቱ በተግባር እየታየ ነው።
የእነዚህ ተግባራዊ ስኬቶች ግንባር ቀደም ማሳያ የሚሆነው በበጎ አድራጊዎች እና በከተማ አስተዳደሮች ቅንጅት ዕውን የሆኑት የምገባ ማዕከላት ናቸው።
ለአብነት ያህል በአዲስ አበባ ከተማ ተገንብተው አግልግሎት እየሰጡ ያሉት ከ30 በላይ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አቅመ ደካሞችን፣ አረጋውያንን እና የጎዳና ተዳዳሪዎችን በቋሚነት እየመገቡ ይገኛሉ።
እነዚህ ማዕከላት የዜጎችን የዕለት ጉርስ ፍላጎት ከመሙላት ባለፈ፣ ማኅበራዊ መተሳሰብን በማጎልበት የአረጋውያንን የነገ ተስፋ ያለመለሙ እና የዜሮ ግቦች ስትራቴጂ መሬት መንካቱን በተጨባጭ ያረጋገጡ ትላልቅ ማኅበራዊ ተቋማት ሆነዋል።
ከምገባ ማዕከላቱ መስፋፋት ጎን ለጎን፣ አቅም የሌላቸው ዜጎች የሚኖሩባቸውን ያረጁ ቤቶች የማደስ እና አዲስ ገንብቶ የማስረከብ ሰፊ የልማት ሥራ የዚህ ማኅበራዊ ንቅናቄ ዋነኛ አካል ነው።
በየዓመቱ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እና በተለያዩ የመንግሥት እና የግል ዘርፍ አጋርነት መርሐ ግብሮች አማካኝነት ለጤና እክል የሚዳርጉ፣ ጣራቸው የሚያፈስስ እና ግድግዳቸው ያዘመመ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰው በአዲስ መልክ ተገንብተዋል።
ይህ ተግባር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችን ከዝናብ እና ከብርድ ከመታደግም በላይ፣ ንፁህና ጤናማ መኖሪያ በማቅረብ ፍትሃዊነትን ያረጋገጠና ለዜጎች ከፍ ያለ ክብር የሰጠ ታሪካዊ ክንውን ነው።
የዜሮ ግቦችን ትግበራ ይበልጥ ዘላቂ የሚያደርገው በጎዳና ወድቀው ለነበሩ ሕፃናት እና ወጣቶች የተፈጠረው የነገ ተስፋ ነው።
አስከፊ በሆነው የጎዳና ሕይወት ውስጥ ሲያልፉ የነበሩ በርካታ ሕፃናት እና ወጣቶች ከየአደባባዩ ተሰባስበው ወደ ተለያዩ ማገገሚያ ማዕከላት እንዲገቡ ተደርጓል።
በእነዚህ ማዕከላት ውስጥም የሥነ ልቦና ድጋፍ ከመስጠት ጀምሮ፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የክህሎት ሥልጠናዎችን በማስታጠቅ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ስኬታማ ሥራ ተከናውኗል።
ይህ ጥረት ከ'ሌማት ትሩፋት' እና መሰል የግብርና ንቅናቄዎች ጋር ተቀናጅቶ፣ ወጣቶች በከተማ ግብርና እና በጥቃቅን ተቋማት ተደራጅተው የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩ አድርጓል።
ሠልጣኞቹ በሥራ ፈጠራ እና በፋይናንስ ድጋፍ ታቅፈው ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ እንዲሁም ሕፃናቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ሲደረግ የልመና እና የተረጂነት አዙሪት በዘላቂነት እየተሰበረ መሆኑን ያሳያል።
እነዚህ የተዋሃዱ የልማት እርምጃዎች ዜጎች በራሳቸው ጥረት እና ምርታማነት ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል።
ዜጎችን ከጎዳና በማንሳት፣ በማዕድ በማጋራት እና መጠለያ በማዘጋጀት የተጀመረው ይህ ጉዞ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ከልመና አረንቋ ወጥተው ራሳቸውን የቻሉ እና አምራች ዜጎች ለመሆን የሚያደርጉትን ርብርብ የሚያፋጥን እና ብሩህ ተስፋን የሚያሰንቅ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: