Search

የተግባር ዘመን፡ በጉባ የተበሠሩት የ30 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶች አሁናዊ አፈጻጸም

ረቡዕ ነሐሴ 20, 2018 37

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባቱ የጉዞ ማጠቃለያ ሳይሆን፣ የአዲስ ምዕራፍ መነሻ መሆኑን በጉባው ታሪካዊ ዕለት መመልከታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በዕለቱም 30 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት የተያዘላቸው ግዙፍ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ይፋ መደረጋቸው ይታወሳል።

ጳጉሜን 4 ቀን 2017 . የኢትዮጵያን የልማት ታሪክ የቀየረ እና ኢትዮጵያውያን በላብ እና በደማቸው የገነቡት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ስኬት በይፋ የተበሰረባት ዕለት ነበረች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በዕለቱ ያስተላለፉት "እኛ ኢትዮጵያውያን ገደሉን ተሻግረን ገድል አትመናል!" የሚለው ጥልቅ መልዕክት ለዘመናት ኢትዮጵያን ተብትቦ የነበረውን የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ድክመት ሰብረን መውጣታችንን የሚያረጋግጥ ነው። የኢትዮጵያ የልማት መስመር በሦስት ታሪካዊ ምዕራፎች ውስጥ አልፏል።

የመጀመሪያው የጥናት እና የህልም ዘመን ሲሆን፣ ከዓመታት በፊት በውጭ ባለሙያዎች የተሠሩ እጅግ ያማሩ ጥናቶች የነበሩበት ወቅት ነበር። ነገር ግን በጂኦ-ፖለቲካዊ ጫና እና በገንዘብ እጥረት በወረቀት ላይ ብቻ ቀርተው፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን እያየን በችግር ለመኖር ተገደድን።

ሁለተኛው የጅምር እና የማነቆ ዘመን ተብሎ የሚጠራው 2000 እስከ 2010 . ያለው ወቅት ነው። በዚህ የጊዜ ክፍል የስኳር ፋብሪካዎች፣ የባቡር መስመሮች እና ሌሎችም ሜጋ ፕሮጀክቶች ቢጀመሩም፣ በሙስና፣ በአስተዳደር ድክመት እና በቴክኖሎጂ ጥገኝነት ምክንያት ፕሮጀክቶቹ ተጓተቱ፤ ብሔራዊ ዕዳንም አባባሱ።

ሶስተኛው የልማት ሉዓላዊነት እና የአፈጻጸም ዘመን ደግሞ 2010 . ወዲህ ያለው ነው። የመደመር አስተሳሰብ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መስመር እንዲይዙ ተደረገ። ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ የገበታ ለሀገር እና የኮሪደር ልማቶችን ጨምሮ፣ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እና በጥራት የመጠናቀቅ ባህል ተፈጠረ።

ላሪ ቦሲዲ እና ራም ቻራን "ኤክሲኪውሽን" በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት አፈጻጸም ራዕይን ወደ እውነታ የሚቀይር ድልድይ ነው። ስኬታማ ፕሮጀክት በርቀት ሆኖ ትዕዛዝ የሚሰጥ አመራር ሳይሆን፣ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በቅርበት የሚመራን አካል ይፈልጋል።

በጉባ የተበሰሩት እና በአሁኑ ወቅት ወደ ተግባር የተለወጡት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ከውጭ ጥገኝነት የሚያላቅቁ እና ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያሸጋግሩ ናቸው።

በየዓመቱ ለማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ በውስጥ የሚያስቀረውና በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ እየተገነባ ያለው የማዳበሪያ ፋብሪካ አንዱ ማሳያ ነው።

ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ወደ ግንባታ የገባው ይህ ፋብሪካ፣ በዓመት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።

አፍሪካን እርስ በእርስ በማስተሳሰር ኢትዮጵያን የዓለም የአቪዬሽን፣ የቱሪዝም እና የካርጎ ማዕከል የሚያደርገው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሌላው ተጨባጭ ዕርምጃ ነው።

በጥር ወር 2018 . በይፋ ግንባታው የተጀመረው ይህ የአቡሴራው ፕሮጀክት፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ ታቅዶ እየተገነባ ያለ የአፍሪካ ትልቁ የነገ አውሮፕላን ማረፊያ ነው።

የኢትዮጵያን የነዳጅ ጥገኝነት በመቅረፍ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣው የተፈጥሮ ጋዝ እና የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክትም በተመሳሳይ ወደ መሬት ወርዷል። በቀን 70 ሺህ በርሜል ነዳጅ ከሂላላ የነዳጅ ክምችት ለማጣራት የሚያስችለው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ግንባታ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ከካሉብ የሚወጣው የተፈጥሮ ጋዝም ለአካባቢው ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እየሆነ ነው።

በአፍሪካ አይታሰብም የተባለውን የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግም የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅንጅት የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን እያፋጠነ ይገኛል።

የከተሞችን ውበት ከመቀየር ባለፈ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ለዜጎች ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የተያዘው ግዙፍ የቤቶች ልማት ፕሮጀክትም ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል የሚከፍት ብሔራዊ ራዕይ ሆኗል።

ዴቪድ ማኩሎው ስለ ፓናማ ካናል በጻፈው መጽሐፍ ላይ አንድ ትልቅ እውነታ አንስቷል። ፈረንሳዮች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር አፍስሰው ያልተሳካላቸውን የፓናማ ካናል ግንባታ፣ አሜሪካውያን ስኬታማ ያደረጉት ችግሮችን ፈትተው፣ ተለዋዋጭ ስትራቴጂ በመጠቀም እና በተጠናከረ አመራር መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያም አሁን እየተገበረች ያለው ይህንኑ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "መደመራዊ የዝላይ መንገድ" በሚል በተገለጸው ጽንሰ-ሐሳብ፣ አውሮፓውያን በመቶ ዓመታት ያለፉትን የዕድገት ደረጃ አቋርጠን፣ የቴክኖሎጂ አቅምን በመጠቀም ፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግር የምናደርግበት ስትራቴጂ ነው።

"አንችልም" የሚለውን የታሪክ ስብራት በማስወገድ የልማት ሉዓላዊነት ተረጋግጧል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ወጥታ የምስራቅ አፍሪካ አልፎም የሙሉ አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የኃይል ማዕከል መሆኗን የሚያረጋግጡ ተግባራዊ እርምጃዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ገደሉን ተሻግራለች፤ ነገ ደግሞ የታላቅነቷን ማማ በዓለም ፊት በትልቅ ግርማ ሞገስ ታቆማለች!

በሲሳይ ደበበ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: