Search

ከተማን እና ገጠርን ያጣመረው ልማት፡ የዛሬዋና የነገዋ ኢትዮጵያ መልክ

እሑድ ነሐሴ 24, 2018 92

የቆሻሻ መከማቻ፣ የበሽታ ምንጭ እና የጨለማ መናኸሪያ የነበሩ ሥፍራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ዓለም አቀፍ የመዝናኛ፣ የቱሪስት መዳረሻና የሥራ ዕድል ፈጠራ ማዕከልነት ተቀይረው በኢትዮጵያ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በኮሪደር እና በወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት በተግባር እየታየ ያለ እውነታ ነው።

የከተሞች ዕድገት እና የከተሜነት መስፋፋት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የብልጽግና መዳረሻ እና የሥልጣኔ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

ከተሜነት የሰው ልጆች ኑሮ የሚቀልልበት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚሟሉበት እንዲሁም ዘመናዊ የሕይወት ዘይቤ የሚሰርጽበት ነው።

ከዚህ ቀደም የነበሩ የልማት አመለካከቶች ከተማን እንደ ሁለተኛ ደረጃ በመመልከት ገጠር ላይ ብቻ ያተኮረ አካሄድ ይከተሉ ነበር።

ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት ከተማን እና ገጠርን ባጣመረ ሁለንተናዊ ዕይታ የልማት ምዕራፉን በአዲስ መልክ ቀይሶታል።

ከተሞችን ማዕከል ያደረገ ልማት የብልጽግና አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ያረጋገጠው ይኸው ፍልስፍና፣ በኮሪደር እና በወንዞች ዳርቻ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች የከተሞችን ገጽታ ከመሠረቱ እየቀየረ ይገኛል።

ከተማ እና ከተሜነት በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በአካባቢያዊ መነጽሮች ሲታዩ ሰፊ ፋይዳ አላቸው።

ከማኅበራዊ አንጻር ከተሞች የቅይጥ ባህል መፍጠሪያ፣ የተለያየ ማንነትና እምነት ያላቸው ዜጎች በስምምነት የሚኖሩባቸው ሕያው ሥፍራዎች ናቸው።

ከኢኮኖሚ አንጻር ደግሞ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ማዕከላት በመሆን ከፍተኛ ሀብት ያመነጫሉ።

ከፖለቲካዊ ዕይታ አንጻር ሲታዩም የዳበረ የዴሞክራሲያዊ ውይይት መሠረት ሲሆኑ፣ ከአካባቢ ጥበቃ አኳያ ከተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ ሥነ ምሕዳርን ለመምራት ያስችላሉ።

የመደመር መንግሥት ለከተሞች በሰጠው ትኩረት ምክንያት ገጠርን የዘነጋ አይደለም፡፡ ይልቁንም አርሶ አደሮችን በአንድ ግቢ በማስተሳሰር የባዮጋዝ፣ የፀሐይ ብርሃን እና የጓሮ ልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ የገጠር ኮሪደር ልማት በቅንጅት እየተተገበረ ነው።

በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች የተተገበረው የኮሪደር ልማት ውበትን ከመፍጠር ባሻገር ሰፊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን አስገኝቷል።

ለበርካታ ዓመታት በቆሻሻ እና በደለል ተውጠው የነበሩ ሥፍራዎች ወደ ተዋቡ የመዝናኛ፣ የካፌ እና የሬስቶራንት ሥፍራዎች ተቀይረዋል።

እንደ እንጦጦ እና ሽሮ ሜዳ ባሉ አካባቢዎች ከሰባት መቶ በላይ አዳዲስ የንግድ መደብሮች ተከፍተው እንጨት በመሸከም ይተዳደሩ ለነበሩ እናቶች እና ሥራ አጥ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

ከዚህም ባለፈ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የጎዳና ላይ መብራቶች እና የደኅንነት ካሜራዎች መዘርጋታቸው ወንጀልን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ የነዋሪዎችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ አስጠብቋል።

በተለይም በአዲስ አበባ የተከናወነው የወንዝ ዳርቻ ልማት ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያ የነበሩትን ወንዞች ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ቻናሎችን በመገንባት ጽዱ እና ማራኪ እንዲሆኑ አድርጓል።

"በአሜሪካ እና በአውሮፓ በወንዞች ዳርቻ የተሠሩ ልማቶችን አይቻለሁ የሚል ሰው መጥቶ የኢትዮጵያን ወንዝ ዳርቻ ቢያይ፣ በፈለገው መስፈርት ካየበት ሀገር የሚሻል እንጂ የሚያንስ ነገር አያይም፤ ይህ ፕሮጀክት ለመላው አፍሪካ ልክ እንደ አረንጓዴ አሻራ ምልክትና ምሳሌ የሚሆን ሥራ ነው" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

በከፍተኛ ቁርጠኝነት፣ በረቂቅ ዕይታ እና ሌት ተቀን በተደረገ ጥረት የተገኘው ይህ ውጤት የመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት ከመሆኑም አልፎ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ዓለም አቀፍ ተምሳሌት ሆኗል።

ዛሬ ላይ በገሀድ የሚታዩት እነዚህ ፕሮጀክቶች ብሔራዊ አቅምን አጉልተው የሚያሳዩ እና የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ መልክ በጽኑ መሠረት ላይ የገነቡ ድንቅ የለውጥ ፍሬዎችም ናቸው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: