ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ታቅፋ፣ ግዙፍ የኢኮኖሚ እምቅ አቅም ይዛ፣ ነገር ግን በጂኦግራፊ ግድግዳ ታጥራ መቅረቷ ከምንም በላይ በውስጧ ለነበሩት እና የነገዋን ብሩህ ተስፋ ለሚመኙት ልጆቿ የዘወትር የሕሊና ቁስል ሆኖ ቆይቷል።
ይህ ብቻም አልነበረም፣ ባለፉት ዘመናት ስለ ባሕር በር እና ስለ ቀይ ባሕር ማንሳት እንደ ታላቅ ኃጢአት ይወገዝ የነበረበት፣ ዜጎች ይህንን ሀገራዊ የሕልውና ጥያቄ ካነሱ እንደ ወንጀለኛ/የሰው ሀገር እንደመውረር ይቆጠርበት እና በሥርዓቱ ጫና ምክንያት ብዙዎች በፍርሃት ተሸብበው ዝምታን የመረጡበት ዘመን ነበር።
ይህ የቆየ የታፈነ ቁስል ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው ከረጅም ዓመታት በፊት፣ በውስጣቸው ሲንተከተክ የነበረ ጥልቅ መንገብገብ እና ቁጭት ነበር።
ወጣቱ ትውልድ በሥራ አጥነት ሲሰቃይ፣ የሀገራችን የንግድ ልውውጥ በአንድ ቀጭን የሎጂስቲክስ በር ላይ ተንጠልጥሎ ሲንገዳገድ፣ ሀገራችን ያላትን ሀብት ወደ ውጭ ማውጣት ሲሳናት፣ እና የሎጂስቲክ ሉዓላዊነቷ በሌሎች እጅ ላይ ሲሆን መመልከት እርሳቸውን ዕረፍት ነስቷቸው ኖሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን የትውልዱን ድምፅ አልባ ጩኸት በሚገባ የተረዱ፣ ያደመጡ እና ያንን የፍርሃት ቆፈን የሰበሩ ደፋር መሪ ናቸው። ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ ያ በውስጣቸው የነበረው ቁጭት፣ የትውልዱን የልብ ትርታ ወደሚያስተጋባ የተግባር ጥሪ ተቀየረ።
ምንም ጥያቄ ማቅረብ በማይቻልበት የፍርሃት ድባብ ውስጥ ተዘፍቆ የነበረውን የትውልዱን ዓይን በመግለጥ፣ አጀንዳውን ማፍረስ እንደ ወንጀል ይቆጠርበት የነበረውን ዘመን ገፈው ጣሉት። እርሳቸው ከፖለቲካዊ መሪነት ባለፈ፣ የታፈነውን የኢትዮጵያውያን የባሕር በር ናፍቆት፣ ታሪካዊ ክብር እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ጥያቄ በድፍረት አደባባይ ያወጡ የዘመናችን ልሳንና ልብ ሆኑ።
የባሕር በር ጥያቄ የሸቀጥ ጉዳይ ሳይሆን የሕልውናችን መሠረት ነው በሚል ጽኑ ዕሳቤ፣ የቀይ ባሕርን ባለቤትነት የመመለስ ትውልዳዊ ተልዕኮ በመቅረጽ ሀገራዊ መነቃቃትን ፈጠሩ።
ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት የነበራቸው ያ ጥልቅ መንገብገብ፣ ሥልጣን ላይ ሲወጡ ወደ ስሜታዊ ዕርምጃ ሳይሆን ወደ በሰለ ስትራቴጂያዊ ተግባር ነው የተቀየረው። ለዓመታት በውስጣቸው ሲብላላ የነበረውን ራዕይ፣ በመጀመሪያ በሰላማዊ ዲፕሎማሲ ለመፍታት የሄዱበት ርቀት እጅግ አስደናቂ ነበር።
ከኤርትራ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት፣ የዚህን ትውልድ የባሕር በር ጥያቄ ከጦርነት እና ከደም መፋሰስ አዙሪት በማውጣት፣ በጋራ ብልጽግና ላይ በተመሠረተ ወንድማማችነት ለመፍታት የተደረገ ብልህ ሙከራ ነበር።
አሰብ ወደብን ከኤርትራ ጋር በጋራ ለማልማት ያቀረቡት ሐሳብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ያን የቆየ ቁጭት እንዴት በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት እንዳሰቡ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ተግባር ነው።
ከዚህም ባሻገር እጅግ የሚያስደንቀው ዕርምጃ፣ ሀገራችን ቀጥተኛ የባሕር በር ሳይኖራት፣ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል በዝምታ እና በጥበብ ዳግም የማቋቋማቸው ስትራቴጂ ነው። ይህ ዕርምጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትውልዱን ሕልም ከሩቅ አሻግረው የሚያዩ መሪ መሆናቸውን በጉልህ ያረጋግጣል።
በወጣትነታቸው ሲሰማቸው የነበረው መንገብገብ፣ ዛሬ ሀገራችን የባሕር ላይ ዘረፋን መከላከል የምትችልበትን፣ የንግድ መርከቦቿን የምትጠብቅበትን እና በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ ውስጥ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ክብሯን የምታስመልስበትን ጠንካራ ጋሻ በማዘጋጀት ተተክቷል።
በዚህ ታላቅ የትውልድ ጥሪ እና መነቃቃት፣ አሁን የቀይ ባሕር አጀንዳ ከግለሰቦች ፍላጎት አልፎ የጸና ብሔራዊ አጀንዳ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፈጠሩትን ይህንን የቀይ ባሕርን የመመለስ ትውልዳዊ ተልዕኮ፣ መላው ዜጋ አዳምጦታል፣ በልቡም አትሞታል።
ያ በፍርሃት ተሸብቦ የነበረ ትውልድ ዛሬ ዓይኑ ተገልጦ፣ መብቱን በድፍረት መሞገት ጀምሯል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይ እና የትውልዱ ድምፅነት፣ ኢትዮጵያን ከጂኦግራፊያዊ እስር ቤት አውጥቶ፣ ክንፏን ዘርግታ በዓለም አቀፍ ደረጃ አየር ላይ እንድትንሳፈፍ የሚያደርግ ስትራቴጂያዊ መንገድ ጠርጓል።
አሁንም ይህ የነቃ ትውልድ በመሪው ጀግንነትና አርቆ አሳቢነት የባሕር መድረሻን ማግኘቱ የማይቀር የታሪክ እውነታ ነው፤ ትውልዱም በጽናት እና በአንድነት ይህንን ብሩህ ሀገራዊ ራዕይ እውን ማድረጉ አይቀሬ ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: