ኢትዮጵያ ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች ይልቅ ለኤሌክትሪክ መኪኖች ቅድሚያ በመስጠት የወሰደችው ታሪካዊ የፖሊሲ ዕርምጃ፣ የትራንስፖርት ሥርዓቱን ከማዘመን ባለፈ የአምራች ኢንዱስትሪውን ገጽታ በአዲስ መልክ እየቀየረው ይገኛል።
ከ90 በመቶ በላይ በውኃ ኃይል ከሚመነጨው ንጹሕ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር የተሣሠረው ይህ አረንጓዴ የትራንስፖርት ሥርዓት የሀገር ውስጥ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ ምቹ መደላድል ፈጥሯል።
በዚህም ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙት እንደ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ፣ ማራቶን ሞተርስ፣ ግሪን ቴክኖሎጂስ፣ ወዳ አውቶሞቲቭ እና የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግ የመሳሰሉ ተቋማት የኢንዱስትሪውን መነቃቃት እያፋጠኑት ነው።
ለአብነትም በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በደብረ ብርሃን እና በገላን ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ኢንቨስትመንት ያቋቋማቸው ፋብሪካዎች በዓመት ከአንድ ሺህ በላይ የሕዝብ ትራንስፖርት እና የጭነት ተሽከርካሪዎችን የማምረት አቅም ፈጥረዋል።
ሌሎችም ኩባንያዎች ከቤት አውቶሞቢል እስከ ቀላል የኤሌክትሪክ ባጃጆች ድረስ ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ፋብሪካዎች ለኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋነኛ ምሰሶ የሆነውን አምራች ኢንዱስትሪ በተጨባጭ እያሳደጉት ይገኛሉ።
ፋብሪካዎቹ ተሽከርካሪዎችን ከመገጣጠም አልፈው ሰፊ የዕሴት ሰንሰለት በመፍጠር ላይ ናቸው።
የጎማ፣ የመኪና መስተዋት፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳ እና የፕላስቲክ ውጤቶችን የሚያመርቱ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለመኪና አምራቾቹ በማቅረብ የገበያ ትሥሥር እንዲፈጥሩ ሰፊ በር ከፍቷል።
ይህ ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገቡ መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የገቢ መተካት ስትራቴጂን እውን እያደረገው ነው።
በተጨማሪም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እየሆኑ ነው።
ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ባሻገር ጥልቅ የሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግርም እየተከናወነ ነው። የመገጣጠም ሒደቱ በከፊል ከተነጣጣሉ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ወደተነጣጣሉ ክፍሎች በማደግ ላይ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዘመናዊ የባትሪ ማኔጅመንት፣ የኤሌክትሪክ ድራይቭ ትሬን ጥገና፣ አውቶሜትድ የታሪፍ መሰብሰቢያ እና የመንገደኞች መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ዕውቀት ለኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች እየተላለፈ ነው።
ይህ ሒደት የሰው ኃይል ክህሎትን ከባህላዊ መካኒክነት ወደ ዘመናዊ አውቶሞቲቭ ሜካትሮኒክስ (mechatronics) በማሸጋገር የዘላቂ ዕውቀት መሠረት ጥሏል።
በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እና በሥራ ማስኬጃ ወጪ ቅናሽ ረገድ የተመዘገበው ውጤትም እጅግ አበረታች ነው።
በአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት መረጃ መሠረት ሰላሳ የነዳጅ አውቶቡሶችን ለማንቀሳቀስ በወር 11 ሚሊዮን ብር ሲወጣ፣ ተመሳሳይ ቁጥር ላላቸው የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች የሚያስፈልገው የኃይል ወጪ 1.5 ሚሊዮን ብር አካባቢ ብቻ ነው።
ይህ ከ86 በመቶ በላይ የሆነ የወጪ ቅናሽ፣ ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ ከማስቻሉም በላይ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ትግል በተጨባጭ ይደግፋል።
ይህ የኢንዱስትሪ ዕድገት የኃይል መሙያ መሠረተ ልማት እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ውሱንነትን የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም፣ መንግሥት የፈቀዳቸው ከቀረጥ ነጻ ማበረታቻዎች እና የኢ-ሞቢሊቲ ስትራቴጂው ለዘርፉ መስፋፋት ምቹ ከባቢ ፈጥረዋል።
አምራቾች ምርቶቻቸውን ወደ ጎረቤት ሀገራት የመላክ ዕቅድ የያዙ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ እና የተሽከርካሪ ኤክስፖርት ማዕከል የመሆን ራዕይዋን እውን ለማድረግ በጠንካራ መሠረት ላይ ቆማለች።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: